በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያሳለፏቸው መመሪያዎችና የጠሯቸው ስብሰባዎች ሕገ ወጥ ተብለዋል ቋሚ ሲኖዶስ፥ የማኅበሩን የፀረ ተሐድሶ ጽሑፍ ጨምሮ የተደረጉትን መጻጻፎች ይመረምራል የፓትርያርኩ ጉዞዎች፥ ስፖንሰር ተገኘ በሚል ሳይኾን በቋሚ ሲኖዶሱ ማስወሰን ይኖርባቸዋል ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ መዋቅር ጠብቀው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑና ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ በቅዱስ ሲኖዶስ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ከቀትር በኋላ ባካሔደው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጽሑፎች ላይ ቀርበዋል ለተባሉ አቤቱታዎች የነበራቸውን አያያዝና የሰጧቸውን ምላሾች ገምግሟል፡፡ ፓትርያርኩ አቤቱታዎቹን ለመመልከት በሚል በራሳቸው የጠሯቸው የኮሌጆችና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች ሓላፊዎች ስብሰባዎች፤ ማእከላዊ አሠራርን ያልጠበቁና አድሏዊ እንደነበሩ ጉባኤው ተችቷል፡፡ ከዚኽም ጋር በተያያዘ ፓትርያርኩ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በተጻፉ በደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያሳለፏቸው መመሪያዎች ሕገ ወጥ መኾናቸውን ያረጋገጠ ሲኾን በስብሰባዎቹ ወጥተዋል የተባሉ የአቋም መግለጫዎችም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተገልጧል፡፡ ፓትርያርኩ ዛሬ ለተጀመረው ዐቢይ ጾም በሰጡት መግለጫ አጋጣሚ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው አማካይነት በጠራው በዚኹ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በኃይለ ቃል ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፤ ማኅበሩንም በተመለሱ ጥያቄዎችና በአሉባልታዎች ወንጅለዋል፡፡ “የማኅበሩ አባላት ናችኹ፤ ሒዱ ስላላችኹ ነው የመጣችኹት” በማለት የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ማኅበሩንም “ሀብታሞች ኾነዋል፤ ከመንግሥትም ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ መንግሥት ይረዳቸዋል፤” እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ተንኮል የተሸረበባቸውንና በክፋት የተሞሉ መረጃዎችን ሳያጣሩና ሳይመዝኑ እንደተነገራቸው የሚያስተጋቡት ፓትርያርኩ፣ እኒኽን ኃይለ ቃላት የተናገሩበት የረፋድ ወኔ ግን አብሯቸው አልዘለቀም፡፡ ስብሰባው ከቀትር በኋላ ሲጀመር አንሥቶ ከፍተኛ መደናገጥ ታይቶባቸዋል፡፡ ማእከላዊ አሠራሩን ሳይጠብቁ የፈጸሟቸውን መተላለፎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ለጉባኤው ያሰሙ ሲኾን በማኅበሩ ላይ ላቀረቡትም ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል፤ የማኅበሩ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ የአባላቱ አስተዋፅኦ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ በሒሳብ አሠራሩም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከማኅበሩ ብዙ የሚማረው እንዳለ አልሸሸጉም፡፡ ለመዋቅራዊ መተላለፋቸውም ኾነ ከማኅበሩ አንጻር ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ያልሰጡት ፓትርያርኩ፣ ማእከላዊ አሠራርን ባለመጠበቅ በፈጸሟቸው ተግባራት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “አዋረዱን፤ አፈርንብዎ” እስከመባል ተገሥጸዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከመዓርገ ክብራቸው አኳያ ከመሰል የደብዳቤ መጻጻፎች እንዲታቀቡ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ በኮሌጆች የሚገኝበትን ደረጃ አስመልክቶ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዳሰሳ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ያወጣውን ጽሑፍ ተከትሎ ፓትርያርኩ የሰጧቸው መመሪያዎችና ከማኅበሩ ጋር የተመላለሷቸው ደብዳቤዎች ይዘት በቋሚ ሲኖዶሱ እንዲመረመር ጉባኤው ወስኗል፡፡ በይቀጥላልም ጉባኤው፣ ፓትርያርኩ በመሰል ጉዳዮች አስፈጻሚ አካላትን በቀጥታ መሰብሰባቸው ስሕተት በመኾኑ፣ ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተነጋገሩና በቋሚ ሲኖዶስ እየመከሩ ሕጉን አክብረውና መዋቅሩን ጠብቀው አመራር መስጠት እንደሚኖርባቸውም በጥብቅ አሳስቧቸዋል፡፡ ግለ ታሪካቸውን ከማበላሸት አልፎ በክፉ ምክሮችና በሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ቤተ ክርስቲያንን እያሳጣና እያስነቀፈ የሚገኘው የልዩ ጽ/ቤታቸው አሠራር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በእጅጉ አሳስቧል፤ የልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና የክፋት ተባባሪዎቹ ጉዳይም አስቸኳይ እልባት እንደሚያስፈልገው ከስብሰባው ውጭ በስፋት የተመከረበትና አቋም የተያዘበት ኾኗል፡፡ የፓትርያርኩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ጉዞ፣ ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ እያወቀው በዕቅድ መከናወን ያለበት ቢኾንም “የራሳችንን ውጭ ሸፍነን ቅዱስነታቸውን እናጅባለን” በሚሉ አማሳኝ ግብረ በላዎች ጭምር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ያለዕቅድ እየወጣ የሚባክንበት፤ ፓትርያርኩ እንደ ርእሰ መንበር ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚወክል ሐዋርያዊ ተልእኮና አባታዊ ሓላፊነት የሚወጡበት ከመኾን ይልቅ “ስፖንሰር ተገኘ” በሚል ብቻ ከፍተኛ ስሕተት(የፕሮቶኮልም) የሚፈጸምበትና ክፋት የሚመከርበት እየኾነ እንደመጣም በጉባኤው ታይቷል፡፡ በመኾኑም የፓትርያርኩ ማንኛውም ጉዞዎችና የሚመደቡ ልኡካን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ሲወሰን እንዲፈጸም ጉባኤው አሳስቧል፡፡ ስለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት በሚመደቡ ልኡካን ተጨማሪ ማጣራት እንዲካሔድ የወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአገራችን ወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይም የመከረ ሲኾን በዛሬው ዕለትም በድንገተኛ ልዩ ስብሰባው ቃለ ጉባኤዎች ላይ በመፈራረም መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡- Hara Tewahido ሐራ ተዋሕዶ
ምንጭ፡- Hara Tewahido ሐራ ተዋሕዶ

No comments:
Post a Comment