Saturday, August 15, 2015

ከድርቁ ይልቅ መግለጫው ያደርቃል!


(የትነበርክ ታደለ)
ትናንት ምሽት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን የጥያቄና መልስ ቆይታ የተከታተለ ሰው እንደ ተለመደው የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ብዥ እንደሚልበት የታወቀ ነው። ጋዜጠኞቹ ራሳቸውን እየጨመቁና እየተሽቆጠቆጡ ለሚያቀብሏቸው ጥያቄዎች ሚንስትሩ ለራሳቸው ብቻ በሚመች መልክ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ብቻ በሚያሳምን መልኩ ምላሽ ሰጥተው ዞር ብለዋል።
ይደንቃል! አሁን አለም በሀገራችን ውስጥ የተከሰተውን ድርቅና ረሀብ በደምብ አብላልቶ እያወራው ነው። ምን ያህል ሰዎችና ከብቶች እንደተጠቁም ከሌሎች የመረጃ ምንጮች ተነግሯል። ረሀብ ገብቷል! ሰው ተርቧል! ከብቶች ሞተዋል! ተጨማሪ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግም የአለም አቀፉ የምግብ ድርጅት ገልጿል።
ይህን ሀቅ ተመርኩዘው መንግስታቸው ችግሩን ቀድሞ ለመቅረፍ ምን አይነት ጥረት እንዳደረገና አሁንም ምን እየተሰራ እንደሆነ ለህዝቡ ግልጽ ማድረግ ሲገባቸው፤ ነገሩን በድብስብስ አልፈውታል።
ሀገራችን ድርቅ ሲገጥማት ይህ የመጀመርያው አይደለም። ደጋግሟታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ቢያንስ በየአስር አመቱ በከፊልም ቢሆን ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ጥናቶች ተጠንተው ተቀምጠዋል። የሀገሪቱ የሜትሮሎጂ ኤጀንሲም ዋናው ስራው ዛሬ ሞቀ ቀዘቀዘ ብሎ እለታዊ ትንበትያ መናገር ብቻ ሳይሆን በየእለቱ የሚሰበስባቸውን መረጃዎች በመጠቀም ሳይንሳዊ በሆነ ሁኔታ የሀገሪቱ ቀጣይ አመታት የአየር ጠባይ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመንግስትም ለአምራቹ ህብረተሰብም ይፋ በማደረግ ቅድመ ዝግጅት ማደረግ ማስቻል ነበር።
ይህንን ግን በቅርብ አመታት ውስጥ አላየንም። የሀገሪቱ ፓርላማም በዚህ ጉዳይ ቁጭ ብሎ የተወያየበት ቀን ትዝ አይለኝም። ይህን ማድረግ ቢቻል ኖሮ ዛሬም ደግመን የወገኖቻችንን የቁም አጽም ባላየን ነበር።
ከሁሉ በላይ የደነቀኝ ደግሞ ዛሬ ምሽት ላይ ሚኒስትሩ የሚሉትን ብለው ካበቁ በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነገሩን ይበልጥ ለማድበስበስ እንደፈለገ በሚያሳብቅ ሁኔታ ወዲያውኑ ስለ ስንዴ ልማት፣ ስለ ምርጥ ከብቶች እርባታና ስለ በምግብ ራስን መቻል ረዥም ሰአት ሰጥቶ ማውራቱ ነው።
ምነው? ሙያዊ ግዴታው ቢቀር የወገኖቻችንን የረሀብ ስቃይ መረዳት እንዴት አይገዳችሁም? እውነት ሀገሪቱ በምግብ ሰብል ራሷን ብትችል ዛሬም ለእርዳታ እጃችንን ምን ያስዘረጋን ነበር? ኧረ መጀመርያውኑስ የረሀብን ወሬ ምን ያመጣው ነበር?
በዚህም አለ በዝያ፤ አሁን ያለውን ሀቅ ዜጎች የመስማት መብት አላቸው። መስማት ብቻም አይደለም መንግስት ችግሩን ለመፍታት ምን ምን እንዳደረግ ጭምር በዝርዝር ሊገለጽ ይገባል። ይህ የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም። የረሀብ ጥያቄ ነው። ያለዝያ አሁንም እነዚያ ቀድሞ ስንወነጅላቸው የነበሩ መሪዎችን ሌጋሲ እያስቀጠልን ነው። ረሀብ ላይ ቀልድ የለም! ህይወትንም ስልጣንንም ይዞ ሄዶ አይተነዋልና!

No comments:

Post a Comment