Tuesday, January 19, 2016

ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግ የደህንነት መ/ቤት ማስረጃ ‹ኦርጅናሉ› እንዲቀርብ አዘዘ


በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በሽብር ከተከሰሱበት በሥር ፍርድ ቤት በነጻ ተሰናብተው አቃቤ ህግ በጠየቀባቸው ይግባኝ ጉዳያቸው በጠ/ፍ/ቤት እየታየ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከብሄራዊ ደህንነት ተገኘ የተባለው የአቃቤ ህግ ማስረጃ ‹ኦርጅናሉ› እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡
በእነ ሀብታሙ አያሌው መዝገብ የተከፈተው ይግባኝ ላይ የተካተቱት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሽ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ እና አቶ አብርሃም ሰለሞን ዛሬ ጠ/ፍ/ቤት ቀርበው ብይን ያገኛሉ ተብሎ ሲጠበቅ ተለዋጭ ቀጥሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ እንዳለው አቃቤ ህግ በስር ፍርድ ቤት አልተመረመረልኝም ያለው ከብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ማዕከል የተገኘው ማስረጃ፣ ማስረጃ ሳይሆን የመረጃ ትንተና የተሰጠበት ስለሆነ ‹ኦርጅናሉ› መረጃ ቀርቦ እንዲመረመር ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
‹‹መረጃው እንደወረደ መቅረብ አለበት፤ ከስልክም ሆነ ከፌስቡክ ወይም ከኢሜል ተገኘባቸው የተባለው ማስረጃ ቃል በቃል ይቅረብ፡፡ ትንታኔ የተሰጠበት ሳይሆን ቀጥታ ቃሉ ይቅረብልን›› ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡
አቶ አብርሃም ሰለሞንን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት የተሰማባቸው 3ኛ የአቃቤ ህግ ምስክር ሙሉ ቃልም አቃቤ ህግ ይዞ እንዲቀርብ ታዝዟል፡፡ ፍ/ቤቱ አቃቤ ህግ የታዘዘውን ማስረጃ ይዞ መቅረቡን ለመጠባበቅ ለጥር 24/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment