Tuesday, February 9, 2016

በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሜቴ የሥርዓቱን የለየለት አምባገነንነትና ቀማኝነትን ተቃውሞ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

 የተሰጠ መግለጫ
በርሃብ እየሞተ ታሞ ስለመዳን የሚያስብ የለም!!!
የአዛኝ ቅቤ አንጓች!
ለሕዝብ ደንታ ቢስ የሆነውና ኃላፊነት የማይሰማው አምባገነኑ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ጤናማውን የሕብረተሰብ ክፍል የመብት ጥያቄ ስላነሱ ብቻ በጥይት እየገደለ፣ እያቆሰለ፣አካለጎዶሎ እያደረገ፣ እየደበደበና በጭካኔ አያያዝ በእስር እያማቀቀ ህክምና እንኳን እንዳያገኙ እየከለከለ ዛሬ ደርሶ ለሕዝብ ጤና የተጨነቀና ያሰበ መስሎ ለመታየት በጤና ዋስትና ስም ከመንግሥት ሠራተኛው፣
ከጡረተኛው፣ ከገበሬውና ከነጋዴው ገንዘብ ለመሰብሰብ የጀመረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ነው።
በአጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይ መምህራን የጤና መድህን ዋስትና አስገዳጅ ሕጉን በመቃወም ፔትሽን እየተራረሙ ለአሰሪ መስሪያ ቤቶች በማስገባት ላይ ይገኛሉ።በደሴ፣ በወልድያ ፣ በአዲስ አበባ፣ በሐረር፣ በአዋሳ፣ በደብረማርቆስ፣ በባሕር ዳር – —በመሳሰሉና በአብዛኛው የአገሪቱ ከተማዎች የሚያስተምሩ መምህራን ከጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው አስገዳጅ የጤና መድህን ዋስትና ለሰራተኛው የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት እስከምን ድረስ እንደሆነ ሠራተኞች ሳይወያዩበትና ፈቃደኞች መሆናቸው ሳይረጋገጥ በአስገደጅ ሕግ ከደመወዛቸው በየወሩ 3% ለመቀነስ በዝግጅት ላይ መሆኑ የሥርዓቱን የለየለት አምባገነንነትና ቀማኝነትን የሚያጋልጥ ነው በማለት ተቃውሞ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ መምህራንም ሆኑ ባጠቃላይም ሠራተኞች በልተው ለማደር በተቸገሩበት ፣ የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጨረሻው ጫፍ ላይ በደረሰበትና የዋጋ ግሽበት (ንረት) እየጨመረ በሚገኝበት ፣በሀገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለረሃብ አደጋ በተጋለጡበትና የወገኖቻቸውን ድጋፍ በሚሹበት ወቅት የጤና መድህን ዋስትና በሚል ሽፋን ከመንግሥት ሠራተኞች በየወሩ 3% ከደመዛቸው ለመቁረጥ መወሰኑ የአዛኝ ቅቤ አንጓች እንዲሉ ነው።ከዚያም በላይ ድብቅ የሆነውን የሥርዓቱን አጀንዳ ለማስፈጸምና ከአዲስ አበባ የተቀናጃ ማስተር ፕላን ጋር በተያየዘ በኦሮሚያ ክልል ፣ ከቅማንት ማንነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ በጎንደር የተነሳበትን የሕዝብ አመጽ አቅጣጫ ለማስቀየር፣ እንዲሁም ያለ በቂ ጥናት የሕዝብን የትኩረት አቅጣጫ ለመለወጥ ተብሎ ከ2010 እ.አ.አ ጀምሮ እየተገነባ ያለው የአባይ ግድብ ግንባታ የገንዘብ ዕጥረትን ለመወጣት አገዛዙ የቀየሰው ዘዴ ከመሆን ባለፈ የሠራተኛው የጤና ሁኒታ አስጨንቆት እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም።
አገዛዙ የአገሪቱን ሀብትና ንብረት እየዘረፈና እያስዘረፈ፣ ሕዝቡን በድህነት አረንቋ ውስጥ እየከተተ ፣ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ነፃነት የሚታገሉ የቁርጥ ቀን ልጆችንና ነፃ ሚዲያን ለማሳፈን በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሰ፣ ለአፋኙ የመከላከያ ሠራዊትና የደህንነት ተቋም ለልማት መዋል የሚገባውን የሀገሪቱን በጀት እያባከነ ላጋጠመው የበጀት እጥረት ማካካሻ ይሆነው ዘንድ በልቶ ማደር ከተሳነው ሠራተኛ በጤና ዋስትና ስም የወር ደመወዙን በአስገዳጅ ህግ ለመቀነስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለሕዝብ ያለውን ንቀትና ማናለብኝነትን የሚያሳይ ነው።
ከዚህ ሕገወጥ የወያኔ ተግባር አንፃር መምህራን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ተቃውሞአቸውን እየገለጹ እንደሆነ ታይቷል።ስለሆነም የደሴ ከተማ መምህራንን ተቃውሞ ለአብነት አቅርበነዋል።
“(1)የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 መሰረት ማለትም የሕግ የበላይነት በሚለው ስር መንግሥት የሚያወጣቸው መመሪያዎች ሕገ መንግሥቱን ከተፃረረ ተቀባይነት እንደሌላው፣”
“(2) በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 43 የልማት መብት በሚለው ስር ብሔራዊ ልማትን በሚመለከት የሚወጡ ፖሊሲዎችና ፕሮጃክቶች ላይ ዜጎች ሐሰባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው የሚል ቢሆንም መንግሥት ሠራተኛውን ሳያወያይ የመድህን ክፍያውያን መጠን ራሱ ወስኖ ማሳወቁ ሕገመንግሥቱን የሚጋፋ መሆኑ፣”
“ (3) በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት መንግሥትም ይሁን ሌላ አካል ዜጎች ያፈሩትን ሀብት የመቀማት መብት እንደሌለው ይገልጻል” ይህ እየታወቀ አገዛዙ ሰራተኞች ተሳትፈው ሳይወያዩበት ከደመዛቸው በግዴታ 3% መቁረጥ የሕግ የበላይነትን መጣስ ነው ብለው በተቃውሞ የፔቲሽን ፊርማቸው አረጋግጠዋል።
ከዚህም በተጫማሪ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በተለይ በዓለም አቀፍ ሠራተኞች ድርጅት ( International Labor Organization, ILO)ስምምነት (Convention) የፀደቁትን መብቶች ማለትም ስራ ማቆም አድማና ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ብሶትን የማሰማት መብት በመጠቀም እንዲዘጋጁና አገር አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ለመምህራንና ለሁሉም ሠራተኞች ጥሪ ያዳርጋል።እስከ መቼ ነው ዝም የምንለው? ምን ቀረብን?
በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ የአገራችን ክፍልና በሌሎች አካባቢዎች እየተደረጉ ያሉት ሕዝባዊ እምቢተኝነት በክልል የተወሰነና የአንድ አካባቢ ችግር መገለጫ ሆኖ እንዳይቀር መፍትሔው በጋራ መነሳትና ትግሉን በማቀናጀት ብሔራዊ አጀንዳ ይዞ የአገሪቱን ሕልውና መጠበቅ የሕዝቡን ነፃነትና አንድነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ እንዲሆን እናሳስባለን ።
በረሃብ እየሞተ ታሞ ስለመዳን የሚያስብ የለም !!!


No comments:

Post a Comment