Thursday, February 11, 2016

የአሜሪካ ውጭ ጉዳት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግስት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን አፈና እንዳሳሰባት ገለፀች


የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ እየወሰደ ያለው አፈናና እስራት አሳስቧት እንደሚገኝ አሜሪካ በድጋሚ ገለጠች።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞም ከፕላኑ ያለፉ ብዙ ጉዳዮችን ያነገበ መሆኑንም የአሜሪካ ውጭ ጉዳት ሚኒስቴር ማክሰኞ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
በተያዘው ሳምንት ሰኞ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸውን የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጆን ክርቢ ሃገራቸው በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተከታተለች እንደሆነ ገልጸዋል።
ይሁንና፣ መንግስት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ቀጥሎ የሚገኘው አፈና አሜሪካንን በጽኑ አሳስቧት እንደሚገኝ ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
እየተወሰደ ያለው የመንግስት እርምጃም ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ከህዝብ ጋር በመወያየት እልባት ለመስጠት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳድር ጆን ከርቢ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ መንግስት አፈናውንና እስራቱን መቀጠሉ ቢያረጋግጡም በዚሁ ዘመቻ ምን ያህል ሰው ለእስር እንደተዳረገና ጉዳት እንደደረሰበት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

No comments:

Post a Comment