Friday, April 8, 2016

የአውሮፓ ህብረት የስደተኞችን ፖሊሲ ሊቀይር ነው


ህብረቱ አዲስ የሚቀይረው ህግ ከተለያዩ ሃገራት ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ የተመለከተ ነው።
አንድ ስደተኛ መጀመሪያ እግሩ ባረፈበት ሃገር ጥገኝነት የመጠየቅ መብት እንዳለው፥ አሁን ያለው የህብረቱ የስደተኞች ፖሊሲ ይደነግጋል።
ይህ የደብሊኑ ስምምነት ግን እየጨመረ ከመጣው የስደተኞች ቁጥር አንጻር ማሻሻያ ያስፈልገዋል ተብሏል።
በዚህም ከ19 90ዎቹ ጀምሮ ስራ ላይ ያለውን ፖሊሲ መቀየርና ማሻሻል መፍትሄ መሆኑን ነው የህብረቱ መግለጫ የሚያሳየው።
የአሁኑን ደንብ ትንሽ ማሻሻል እና በብዛት ስደተኛ የሚቀበሉ ሃገራትን መደገፍና ማገዝ አንዱ አማራጭ ይሆናልም ነው የተባለው።
አልያም ከፖሊሲ ማሻሻያ ጋር ስደተኞችን ለሃገራት እኩል ማከፋፈልም ህብረቱ ሊከተለው የሚችለው አማራጭ ነው እየተባለ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የህብረቱ አባል ሃገራት የትኛውም አይነት አማራጭ እንደማይዋጥላቸው ገልጸዋል።
ምክንያቱም በቀደመው ደንብ መሰረት ስደተኞች ጥገኝነት የሚጠይቁት እግራቸው መጀመሪያ በረገጠበት ሃገር እንጅ ድንበር ተሻግረው ያረፉበት ሃገር አይደለምና።
በደብሊኑ ደንብ መሰረትም ጥገኝነት የጠየቁ ስደተኞችን ከሃገራቸው የማስወጣት እና ያለማስጠለል መብት አላቸው።
የጥገኝነት ጥያቄው መጀመሪያ እግራቸው የረገጠበትን እንጅ የገቡበትን ሃገር አይመለከትምና።
ይህን ደግሞ ብሪታንያን ጨምሮ በርካታ ሃገሮች ይፈልጉታል።
እናም የትኛውም አይነት አማራጭ ቢቀርብ የቆየውን ህግ ብቻ መተግበር ምርጫቸው እንደሆነ ነው ሃገራቱ የገለጹት።
በሳምንቱ መጀመሪያ ከመካከለኛው ምስራቅ ቱርክን ተጠቅመው ግሪክ የደረሱ ስደተኞችን ወደ ቱርክ የመመለሱ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።
202 ስደተኞችም ከግሪኳ የሌዝቦስ ደሴት ቱርክ ዲኪሊ ደርሰዋል።
በርካታ የአውሮፓ ሃገራትም የስደተኞችን ፍልሰት ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ድንበራቸውን ከመዝጋት ጀምሮ የተጠናከረ ጥበቃ ማድረግና ለመግባት የሚሞክሩትን ባሉበት ማቆየት የሚጠቀሱ እርምጃዎች ናቸው።
ምንጭ፦ ቢቢሲ

No comments:

Post a Comment