Saturday, March 14, 2015

‹‹በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው ቅራኔ አገርን እስከማፍረስ ሊሄድ የሚችል ነው››


‹‹በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው ቅራኔ አገርን እስከማፍረስ ሊሄድ የሚችል ነው››
አቶ ልደቱ አያሌው፣ የኢዴፓ መሥራችና የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል
አቶ ልደቱ አያሌው የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራች ሲሆኑ፣ ለረጅም ጊዜ ፓርቲውን በመምራት በፖለቲካው መድረክ ባደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ይታወቃሉ፡፡
አቶ ልደቱ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በታሪክ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፓርቲው በአቶ ሙሼ ሰሙና በዶ/ር ጫኔ ከበደ ሲመራ አቶ ልደቱ እንደከዚህ ቀደሙ ንቁ ተሳታፊ መሆን አልቻሉም፡፡ እርግጥ ለዚህ አንዱ ምክንያት ለሁለት ዓመታት በዴቨሎፕመንት ስተዲስ መስክ በእንግሊዝ ለንደን ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ መቆየታቸው ነው፡፡ ይሁንና የግል የፖለቲካ ገጠመኞቻቸውንና ተግዳሮቶቻቸውን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ ጥልቅ ትችት የሚያቀርቡና ግምገማ የሚያደርጉ መጻሕፍትን ማሳተም ቀጥለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹የአረም እርሻ›› እና ‹‹መድሎት›› የተሰኙ መጻሕፍት ያሳተሙት አቶ ልደቱ በቅርቡ ደግሞ ‹‹ቴአትረ ቦለቲካ›› የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ አቅርበዋል፡፡ በዚሁ አሉባልታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ስላለው ተፅዕኖ በሚያብራራው መጽሐፍና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ሰለሞን ጎሹ አወዛጋቢውን የፖለቲካ ሰው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አቶ ልደቱ ከፖለቲካ መድረኩ ጠፍተዋል የሚል አስተያየት ይደመጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
አቶ ልደቱ፡- እንደዚያ ዓይነት አስተያየት እንደሚሰጥ አውቃለሁ፡፡ እኔ ግን አልተጠፋሁም፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል በለንደን ትምህርት ላይ ነበርኩ፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ በፓርቲው ውስጥ የነበረኝን የመሪነት የጊዜ ገደብ ጨርሼ ነበር፡፡ ስለዚህ ሌላ ሰው [አቶ ሙሼ ሰሙ] ተተክቶ ነው የሄድኩት፡፡ ከዚያ በኋላ በሥራ አስፈጻሚ አባልነት እየተሳተፍኩ አይደለም፡፡ በማዕከላዊ ምክር ቤት አባልነት ግን እየሠራሁ ነው ያለሁት፡፡ አሁን ፓርቲው ውስጥ ያለኝን ኃላፊነት ሊመጥን የሚችል ሥራ እየሠራሁ ነው ያለሁት፡፡ ብዙ ጊዜ የፓርቲውን የዕለት ተዕለት ሥራ የሚመሩትና የፓርቲውን እንቅስቃሴ በተመለከተ መግለጫ የሚሰጡት የሥራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው፡፡ ስለዚህ አልጠፋሁም፤ ወደፊትም የመጥፋት ሐሳብ የለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ‹‹ቴአትረ ቦለቲካ – አሉባልታና የአገራችን የፖለቲካ ገመና›› የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ከምክንያታዊና በዕውቀት ላይ ከተመሠረተ ውሳኔ ይልቅ አሉባልታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተሻለ ቦታ እንዳለው ተከራክረዋል፡፡ ምክንያቱ  ለምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- ትግሉን ከመቀላቀሌ በፊትና ወደ ትግሉ ስገባ በነበረኝ አመለካከት ከፖለቲካ አንፃር አሉባልታ ያን ያህል ከባድ ችግር ነው ብዬ አላይም ነበር፡፡ ብዙ ሰው አሁንም እንደዚያ የሚያስብ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ወደ ትግሉ ከተቀላቀልኩ በኋላ በነበረኝ ረጅም ቆይታ በዋናነት ከባድ ፈተና ሆኖ ያገኘሁት የአሉባልታን ጉዳይ ነው፡፡ አሉባልታ በጣም ሥር የሰደደና በፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በኅብረተሰብ ደረጃም የሚገኝ መሆኑን ነው መረዳት የቻልኩት፡፡ ለምሳሌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ አጀንዳ ኖሮን በአንድነት መቆም አልቻልንም፡፡ ልዩነት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ በምንላቸው ጉዳዮች በጋራ እንዳንሠራ ካደረጉን ጉዳዮች አንዱ አሉባልታ ነው፡፡ አንዱ ፓርቲ ሌላውን ፓርቲ ይጠላል፡፡ የሚጠላበት የተጨበጠ ምክንያት ግን የለም፡፡ የሚጠላው አብዛኛውን ጊዜ ከስም ማጥፋትና ከአሉባልታ በመነሳት ነው፡፡ ይኼ ትግሉ እንዳይጠናከር ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲም የውስጥ ችግሩን ፈቶ የቆመለትን ዓላማ መሠረት አድርጎ ትግሉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደይችል ያደረጉ በአመራር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሁሉ መነሻቸው በአብዛኛው ከአሉባልታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ ነው የሚያፈርሰንና የሚከፋፍለን የሚል ክስ ሲያቀርቡ እሰማለሁ፡፡ ገዥው ፓርቲም የሚያፈርሰን ከሆነ በመካከላችን አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲያይ፣ አንዱ በሌላው ላይ ተገቢ ያልሆነ አሉባልታ እንዲያዛምትና ቅስቀሳ እንዲያካሂድ በማድረግ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ከዚያ በላይ ግን ብዙ ጊዜ ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮችና በአሉሽ አሉሽ ከአንድ ሰው የተጀመረው አሉባልታ በከፍተኛ ደረጃ አድጎ የፓርቲ ችግር የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንድ አሉባልታዎች በኅብረተሰቡና በፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክሩበትን ሁኔታም አይቻለሁ፡፡ በፓርቲዎቹ የሚፈጠሩ ችግሮችን ጤናማ በሆነ ውይይት በመፍታት ወደተሻለ ጥንካሬ እንዳያመሩም አድርጓል፡፡
በገዥውና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከልም በጣም የጦዘ ቅራኔ እንዲኖር በማድረግም ረገድ አሉባልታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ውጭ አገር ባለውና በፖለቲካው ዙሪያ መሳተፍ እፈልጋለሁ በሚለው ኃይልና አገር ውስጥ ባለው መካከል ያለው ግንኙነት ጤነኛ እንዳይሆን የአሉባልታ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይኼ የአሉባልታ ችግር ካልተፈታ በስተቀር የተቃውሞ ትግሉ የትም ሊደርስ እንደማይችል ተረድቻለሁ፡፡ እኔም መጽሐፉን የጻፍኩት ኅብረተሰቡ ይህን ችግር እንዲረዳ ነው፡፡ ዙሮ ዙሮ የፖለቲካ ትግሉ ይቀጥላል፡፡ አዳዲስ ኃይል ወደ ፖለቲካ ትግሉ መግባቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ወደ ፖለቲካ ትግሉ የሚገባ አንድ ሰው የሚጠብቀው ችግር በተለምዶ ሌላ ነው፡፡ አሉባልታ ትልቅ ፈተና ይሆንብኛል ብሎ አይጠብቅም፡፡ ስለዚህ መጠበቅ እንዳለበትና ይኼን አውቆ ራሱን ማዘጋጀት እንዲችል መጽሐፉ አንድ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዋናነት ወጣቱ ትውልድ ወደፊት ወደ ፖለቲካው ትግል ሲገባ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሉባልታ ያለውን ቦታና ተፅዕኖ በደንብ ተረድቶ ቢገባ ለትግሉ መጠናከር ይረዳል፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ወደ ተሻለ የሠለጠነ ባህል እንድሄድ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል ነው የጻፍኩት፡፡
ሪፖርተር፡- በመጽሐፍዎ ላይ አሉባልታዎች እውነት መስለው እንዲታዩ በማድረግ መነሻ የሆነውና በማሠራጨት ትልቅ ሚና የሚጫወተው ሚዲያ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ረገድ እርስዎ ንቁ ተሳትፎ ባደረጉበት ያለፉት 22 ዓመታት የሚዲያው ተሳታፊዎችና አወቃቀሩ ላይ ለውጥ አይተዋል?
አቶ ልደቱ፡- ስለሚዲያም ስናወራ እዚያ ውስጥ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚያ ሰዎች ደግሞ ከኅብረተሰቡ የወጡ ናቸው፡፡ አሉባልታ ኅብረተሰባችን ውስጥ በደንብ ሥር የሰደደ ችግር መሆኑን የሚያሳየው አንዱ ነገር በጋዜጠኝነት ሙያ የተሰማሩ ሰዎችም የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸው ነው፡፡ አንድ ግለሰብ አሉባልተኛ ቢሆን በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው ችግር ብዙም ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ ድርጅት አሉባልታ አራማጅ ቢሆን ከግለሰብ ላቅ ባለ መልኩ ችግሩን ማስፋት ቢችልም፣ በኅብረተሰብ ደረጃ በጣም ችግር ላይፈጥር ይችላል፡፡ ግን አንድ ሚዲያ የአሉባልታ ሰለባ ከሆነ የሚፈጥረው አደጋ ቀላል አይሆንም፡፡ በቀላሉ በኅብረተሰቡ ውስጥ መድረስ የሚችል ነው፡፡ ብዙዎቹ በሚዲያ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከዚህ ችግር የፀዱ አልነበሩም፡፡ ሚዲያ እውነት ያልሆኑ ነገሮች ሲነሱ ተገቢ ክትትል አድርጎ እውነቱን ለኅብረተሰቡ የማሳወቅና የማጋለጥ ሚና እንዲጫወት ነው የሚጠበቀው፡፡ ነገር ግን አሁን ብዙዎቹ በሥራ ላይ ባይሆኑም አሉባልታን የሚያስፋፉ ነበሩ፡፡ ኅብረተሰቡ ደግሞ ለዴሞክራሲና ለፕሬስ አዲስ ስለነበር በሚዲያ ላይ የቀረበ ሁሉ እውነት እንደሆነ አድርጎ የማሰብ ውስንነት ነበረው፡፡ ይኼን የኅብረተሰቡን ድክመት በመጠቀም አንዳንድ ጋዜጠኞች ብዙ ችግር ፈጥረዋል፡፡ በፖለቲካ ረገድ ያለው ቅራኔ በዚህ ደረጃ የሰፋ እንዲሆንና ወደ ተሻለ የመቻቻል ፖለቲካ መሄድ እንዳንችል ያደረገን አንዱ ምክንያት ሚዲያው የዚህ ችግር ሰለባ መሆኑ ነው፡፡ አንድ አሉባልታ ሲነሳ ከየት መጣ ተብሎ በጋዜጠኞች አይጠየቅም፡፡
ስለዚህ የነበረው አጠቃላይ የሚዲያ አሠራር አሉባልታ የሚያዛምቱ ሰዎችን የሚያበረታታ ነበር፡፡ አሁንም ከዚያ ዓይነቱ አሠራርና አስተሳሰብ ያልተላቀቁ እንዳሉ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ባለፉት 15 ዓመታት ከነበረው አንፃር ሲታይ ኅብረተሰቡ አንዳንድ ነገሮችን በተሻለ ይረዳል፡፡ የተጻፈው ነገር ሁሉ እውነት ነው ብሎ አያምንም፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ የተደረሰው ብዙ ዋጋ አስከፍሎ ነው፡፡ በመጽሐፌ ላይ የእኔን ስም በተለያዩ ጊዜያት በማጥፋት ረገድ ተሳትፎ የነበራቸው በርካታ ሚዲያዎችን ለአብነት ጠቅሻለሁ፡፡ ከሌላ ተቀብለው በማሠራጨት ብቻ ሳይሆን ራሳቸው አሉባልታ የፈጠሩ ሚዲያዎችም ነበሩ፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት በጻፏዋቸውና በአዲሱ መጽሐፍዎም ላይ የፖለቲካ ጽንፈኝነት ትልቅ ችግር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የጠቀሱት ዋና ጉዳይ የትውልድ ልዩነትን ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሚገባውን ያህል እንዲሠራ ዕድል እንዳልተሰጠው ተከራክረዋል፡፡ ፓርቲዎ ኢዴፓ በቅርቡ ባወጣው ማኒፌስቶም ትኩረቱን በወጣቱ ላይ አድርጓል፡፡ ወጣቱ ተገሏል የምትሉበት ዋና ምክንያት ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- በአንድ በኩል ከፖለቲካ ፅንፈኝነት ጋር በተያያዘ ይኼ ችግር ከየት ነው የመጣው የሚለውን ማሰብ የግድ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ችግሩ እንዴት፣ ለምንና መቼ ተፈጠረ የሚለውን ነገር ወደኋላ ሄዶ የመመርመር አዝማሚያ አይታይም፡፡ ለምሳሌ ስለኢሕአዴግ አምባገነንነት ደግመን ደጋግመን እናወራለን፡፡ ኢሕአዴግ እንዴትና ለምን አምባገነን ሊሆን ቻለ ብለን አንመረምርም፡፡ ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግር በተመሳሳይ እናወራለን፡፡ ነገር ግን ለምን የዚህ ችግር ሰለባ ሆኑ የሚለውን ግን ወደኋላ መለስ ብለን መሠረታዊ የሆነውን የችግሩን ምንጭ ለመመርመር አንሞክርም፡፡ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የመንግሥትነት ታሪክ ያላት አገር ናት እንላለን፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ሁኔታችን በጥላቻና በመናቆር የተሞላ ነው፡፡ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ ሲገዳደሉባት የነበረች አገር ናት፡፡ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ተፈጥሯዊ ሆኖ እያለ፣ አንድ ትውልድ ሊባል የሚችል ኅብረተሰብ ያለቀባት አገር ነች፡፡ አሁንም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ነው የምናራምደው እያልን የፖለቲካ ቅራኔው ቀጥሏል፡፡ ምናልባት ነባራዊና አካባቢያዊ ሁኔታው አልተመቻቸው ሆኖ ይሆናል እንጂ፣ ጠብመንጃም አንስተው መገዳደል የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች አሁንም አሉ፡፡ ለምን እንደዚህ ሆንን ብዬ ለመጠየቅ ስሞክር በዋናነት መሠረታዊ ችግር ሆኖ ያገኘሁት ይኼ ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ያለፍንበት የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ያመጣብንን ጣጣ ነው፡፡ እነዚያ ኃይሎች አሁንም ፖለቲካው ውስጥ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ድርጅታቸውን ስም ቀይረዋል፡፡ ግን ሰዎቹ አልተቀየሩም፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ገዥው ፓርቲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ውስጥም ይገኛሉ፡፡ ተቃዋሚውንም ሆነ ገዥውን ፓርቲ በመደገፍ ተሳትፎ የሚያደርገው ኅብረተሰብ ውስጥም እናገኛቸዋለን፡፡
ከፖለቲካ ውጪ ማኅበራዊ ሕይወትም ውስጥ በጣም ተደማጭነት ያላቸውና የወሳኝነት ሚና ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ይኼ የኢሕአፓመኢሶን ትውልድ የምንለው ነው፡፡ ፖለቲካችን ጤናማ፣ የመቻቻል፣ የመደራደርና የሰጥቶ መቀበል እንዳይሆን ያደረገው ዋና ምክንያት ይኼ የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ነው፡፡ የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ሁለት ሦስት አማራጮች አይቀበልም፡፡ የእኔ መስመር ብቻ ትክክል ነው የሚል ነው፡፡ ከእኔ አስተሳሰብ ውጪ የሆነ ሁሉ መኖር የለበትም፣ መጥፋት አለበት የሚል ነው፡፡ ይኼ ችግር የትናንቱን ብቻ ሳይሆን የዛሬውንም የፖለቲካ ሁኔታ እየወሰነ ነው ያለው፡፡ እዚህ ጋ መቆም ካልቻለ የነገውንም የፖለቲካ ሁኔታ ይወስናል፡፡ ሁለተኛ ይኼ አገር የሕዝቡን ቅንብር ወይም መልክዓ-ሕዝብ (ዴሞግራፊውን) ስናጠና የወጣት አገር ነው፡፡ 70 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ ነገር ግን በፖለቲካው ረገድ ቁልፍ የሆነውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት በኢሕአፓ – መኢሶን ዘመን የነበሩት ሰዎች ናቸው፡፡ ሕወሓትን ያቋቋሙት ሰዎች ዕድሜ ከ18 እስከ 22 ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ናቸው አሁንም በ60 ዓመታቸው አመራር ላይ ያሉት፡፡ የአሁኑ ትውልድ ግን አይደለም በ20 ዓመቱ በ30 እና በ40 ዓመቱም የፖለቲካ መሪ መሆን አልቻለም፡፡ ተከታይ ነው የሆነው፡፡ ሲነገርለትና ሲጻፍለት የኖረውን ያን ትውልድ የሚያሞካሽ ነው፡፡
ያ ትውልድ ጥሩ ትውልድ አይደለም እያልኩ አይደለም፡፡ በብዙ መንገድ ሊመሰገን የሚገባ ባህርይ አለው፡፡ ለሕይወቱ የማይሳሳ፣ ለቆመለት ዓላማ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል የሚችል ትውልድ ነው፡፡ ግን ደግሞ ይኼን በጎ ነገር ያ ትውልድ ይዟቸው ከመጣው መጥፎ ነገሮች ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ያ ትውልድ በዚያን ጊዜ ይከተለው የነበረው ርዕዮተ ዓለም ትክክል ነበር ወይ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ያ ትውልድ የራሱን የፖለቲካ ሚና ይዞ የራሱን ዕድል በራሱ ወስኗል፡፡ ይኼ ትውልድ ግን እየወሰነ አይደለም፡፡ እነሱ ናቸው አሁንም እየወሰኑለት ያለው፡፡ አሁን ያለውን ትውልድ የተለያየ መልክና ስም እየሰጡ እያንኳሰሱት ነው፡፡ እኔ ይኼ ትውልድ የራሱን ሚና መጫወት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ የማይስማሙ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ቢያንስ ግን ይኼ ጉዳይ ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡ አሁን የጻፍኩት መጽሐፍ ሦስተኛዬ ነው፡፡ በመጽሐፎቼ ይዘት ላይ አንድም የፖለቲካ ሰው ትችት ሲያቀርብ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ያን ትውልድ መተቸት እንደ ትልቅ የፖለቲካ ነውር ነው የሚቆጠረው፡፡ ይኼ መሰበር መቻል አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከርቀት የመቆጣጠር ፍላጎት እንዳለውና አገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ኃይል ነፃነት እንደሚጋፉ ጽፈዋል፡፡ ተፅዕኖውን መቋቋምና አብሮ መሥራት እንዴት አልተቻለም?
አቶ ልደቱ፡- ውጭ አገር ያሉ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በግራ ፖለቲካ የሚመሩ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በደርግ ዘመን በተለያየ የፖለቲካ ምክንያት አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ የተገደዱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በ1960ዎቹ ገና ደርግ ሥልጣን ሲቆናጠጥ አገር ጥለው የሄዱ ናቸው፡፡ የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች ደግሞ በዚህ ሥርዓት ዘመን የወጡ ናቸው፡፡ ኅብረተሰባችን ውጭ ላሉ ሰዎች የራሱ የሆነ በጎ አመለካከት አለው፡፡ የተማሩና ዕውቀት ያላቸው ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ውጭ የሚኖሩ ሰዎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሥርዓት ውስጥ ስለሚኖሩ ስለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት የተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል ብሎ ያስባል፡፡ ውጭ ያሉ ሰዎች የተሻለ የመሥራት ዕድል ስለነበራቸው የተሻለ የገንዘብ አቅም ይኖራቸዋል ብሎ ያምናል፡፡ ኅብረተሰቡ ውጭ አገር ላሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ያለው አመለካከት መሆን ከሚገባው በላይ ቀና ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ተፅዕኖአቸው ቀላል አይደለም፡፡ እነሱ የሚያሠራጩት ነገር በቀላሉ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ዕድል አለው፡፡ ይኼ ነገር ትናንት እንደነበረው ዛሬም ቀጥሏል ማለት አይቻልም፡፡ ለውጦች አሉ፡፡ ብዙው ሕዝብ ግን አሁንም ለአገሪቱ ጥሩ ነገር የሚያመጡ ሰዎች ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ እንደዚያ ዓይነት አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን በድርጅት ደረጃ አብዛኛዎቹን ካየን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካ ችግር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ለዚህ የገንዘብ አቅማቸውን ይጠቀማሉ፡፡ አገር ቤት ያለው ኅብረተሰብ በገንዘብ ፓርቲዎችን የመርዳት ባህሉ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርቲዎች ያለባቸውን የገንዘብ ችግር ለመሙላት ውጭ አገር ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ይፈጥራሉ፡፡ ያ ገንዘብ ሲመጣ ዝም ብሎ አይመጣም፡፡ አብሮት አጀንዳና አስተሳሰብ ይመጣል፡፡ ይኼ እዚህ አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት እንዳይሠሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ውጭ አገር ያሉ ሚዲያዎችም የእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች መጠቀሚያ ናቸው፡፡ በእነዚያ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት የሚያስተላልፉት መልዕክት እዚህ ኅብረተሰቡ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያዋጣን የሚችለው ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው ብሎ እንዳያምን በማድረግ ረገድ እነዚህ ሚዲያዎች በጣም ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ ሰው በሙሉ ልቡ ሰላማዊ ትግሉን እንዳያጠናክርና በዚያ ውስጥ ተሳታፊ እንዳይሆን በማድረግ ረገድ ተፅዕኖአቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ኢዴፓ ያደረገው ነገር በገንዘብ መርዳቱን እርዱን ነገር ግን የፖለቲካ አመለካከታችሁን ልትጭኑ አትችሉም ነው ያለው፡፡ ይህን በማድረጋችን በውጭ አገር የምናገኘው ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡ ሌሎችም ፓርቲዎች ከዚህ ሁኔታ ካልወጡና በራሳቸው መሥራት ካልጀመሩ፣ ወይም ደግሞ ከተፅዕኖ ነፃ ሆነው መሥራት ካልጀመሩ፣ ወይም አገር ቤት ያለው ኅብረተሰብ ይህን ችግር አውቆ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በቂ የሆነ ዕርዳታ ካልሰጠና ነፃነታቸውን እንዲያስከብሩ ካላደረገ፣ ፖለቲካው አሁንም በሌሎች ተፅዕኖ ሥር መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ውጭ ያለው ኃይል ምርጫ በመጣ ቁጥር ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫ እንዲያገሉ ነው የሚጠይቀው፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ አንዳንድ በጎ ነገሮች እንኳን ቢኖሩ እነሱን ማድነቅና ማመስገን እንዳይቻል የሚያደርግ የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው የሚያራምዱት፡፡ አሉባልታንም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከውጭ ወደ ውስጥ በማዛመት የሚጫወቱት ሚናም ቀላል አይደለም፡፡ ውጭ ያለው ኃይል የፖለቲካ ትግሉን ሊመራ አይገባም፡፡ አጋዥ ነው መሆን ያለበት፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ በግልዎ በተደጋጋሚ የሚያንፀባርቁት ሐሳብና ፓርቲዎም አቋም አድርጎ የያዘው በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ከመያዝ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ መታገል እንደሚያስፈልግ ይገልጻል፡፡ በገዥው ፓርቲ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በኅብረተሰቡ በአጠቃላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያሻቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ልደቱ፡- ዴሞክራሲን በጠብመንጃ ማምጣት አይቻልም፡፡ አንድ ሰው በጦርነት ሒደት ውስጥ አልፎ ለሥልጣን ከበቃ በኋላ በዴሞክራሲ አግባብ ሥልጣን የመልቀቅ ዕድሉ በጣም የጠበበ ነው፡፡ አንድ ድርጅት ወደ ሥልጣን መምጣት የሚችለው፣ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥትም ከሥልጣን መውረድ የሚችለው በምርጫ ብቻ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በዚህ ረገድ የጠራ አቋም አልያዙም፡፡ ሰላማዊ ትግል አማራጭ አይደለም ብሎ የሚያስብ ቀላል የማይባል የፖለቲካ ኃይል አለ፡፡ ይኼ የፖለቲካ ኃይል የራሱ የሆነ ደጋፊ ኅብረተሰቡ ውስጥ አለው፡፡ ኅብረተሰቡ በዚህ ረገድ ልቡ ለሁለት በተከፈለበት ሁኔታ ሰላማዊ ትግሉ የሚገባውን ያህል ተጠናክሮ ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ችግራችን በመንግሥት ለውጥ ብቻ አይፈታም፡፡ በመንግሥት ለውጥ ችግር የሚፈታ ቢሆን ኖሮ መንግሥት በለወጥን ቁጥር የኢትዮጵያ ችግር በተፈታ ነበር፡፡ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የኅብረተሰቡን ጥቅም የሚያስከብሩ ተቋማት መገንባት አለባቸው፡፡ ይኼ ነው ዴሞክራሲን በዘላቂነት ሊያመጣ የሚችለው፡፡ እስካሁን ድረስ የነበረው አስተሳሰብ የችግሩ ምንጭ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነው፣ እሱ ከሥልጣን ሲወርድ ችግሮች ሁሉ ይፈታሉ የሚል ነው፡፡ በእኛ እምነት ይኼ አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የራሱ የሆኑ ችግሮች ቢኖሩበትም፣ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ግን እሱ ነው ብለን አናምንም፡፡ አንዳንዳቹ ችግሮች መሠረታዊ የሆኑ የኅብረተሰብ ችግሮች ናቸው፡፡ በእያንዳንዳችን ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሲጠፋ አብረው የሚጠፉ አይደሉም፡፡ ከአንድ መንግሥት መውደቅም በኋላ ችግሮቹ ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሊባባሱም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ረገድ ያላቸው አቋም ሊቀየር ይገባል፡፡ ገዥውን ፓርቲ የችግሩ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔውም አካል አድርገን ማየት አለብን፡፡ ተቃዋሚው የሚፈልገው ኢሕአዴግ ተጠራርጎ ጠፍቶ ሌላ አዲስ ሥርዓት መመሥረት ነው፡፡ ሌላ አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ነው የሚፈልገው፡፡ አዲስ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነው የሚፈልገው፡፡ በዚህ መፍትሔ ሊመጣ አይችልም፡፡ ውጤቱ ሌላ አኩራፊ ወይም አማፂ መፍጠር  ነው የሚሆነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፀረ ሕዝብና ፀረ ሰላም እያለ በመፈረጅ የችግሩ ሁሉ ምንጭ ተቃዋሚው ጎራ እንደሆነ አድርጎ ያሳያል፡፡ ራሱን ከችግሩ የፀዳና ለአገሪቱ ችግር ብቸኛ መፍትሔ አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይኼ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሰሞኑን የሕወሓት 40ኛ ዓመት እየተከበረ ነው፡፡ በየመገናኛ ብዙኃኑ የምንሰማው ከውልደቱ እስካሁን ድረስ ያልተሳሳተ ድርጅት እንደሆነ ነው፡፡ የሚሠራቸው ነገሮችና የሚከተላቸው መስመሮች ሁሉ የጠሩና የበቁ እንደሆኑ ነው የተነገረን፡፡ ከእሱ በተቃራኒ የቆሙ ኃይሎች ሁሉ ግን በስህተት የተሞሉ እንደሆነና የጥፋት መልዕክተኞች እንደሆኑ ተደርጎ ነው የቀረበው፡፡ ይኼ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት እውነት ቢሆን ኖሮ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አያስፈልግም ነበር፡፡ በፖለቲካ ሒደት ፍፁም እውነት ፍፁም ስህተት የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሉም አንፃራዊ  ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ይኼንን ማመን እስካልቻለ ድረስና አሁንም እኔ ብቻ ነኝ የችግሮች መፍትሔ ብሎ ካመነ በዚህ አገር ዴሞክራሲና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎችን እንደ ጠላትና የአገር አፍራሽ አድርጎ የማየት አስተሳሰቡን ማቆም አለበት፡፡ በኢትዮጵያ የተቃዋሚዎች ሚና ወሳኝ እንደሆነና ምትክ የሌለው እንደሆነ ማመን አለበት፡፡ አሁን ያለው የኢሕአዴግ አስተሳሰብ ከግራ ፖለቲካ የመነጨ ነው፡፡ እንደርስበታለን የሚባለው የካፒታሊስት ወይም የሊበራል አስተሳሰብ ነው፡፡ ፖለቲካችን ግን እየተካሄደ ያለው በግራ ፖለቲካ ነው፡፡ ይኼ መቆም አለበት፡፡ ኅብረተሰቡ ተቃዋሚና ገዥ ፓርቲዎችን የሚመዝንበት መንገድ የጠራ መሆን አለበት፡፡ አንድን የፖለቲካ ፓርቲ መመዘን ያለበት በሌላ መንገድ ሳይሆን በያዘው አማራጭ ፖሊሲ ብቻ መሆን አለበት፡፡ የእኔን ሕይወት በምን መልኩ ሊለውጠው አስቧል? አጠቃላይ የአገሪቱን ህልውና በተመለከተ ምን አዲስ አማራጭ ሐሳብ ይዞ መጥቷል? ብሎ ከራሱ ጥቅም ጋራ ፖለቲካን ማስተሳሰር መቻል አለበት፡፡ አሁን ግን አብዛኛው ኅብረተሰብ ድጋፍ የሚሰጠው በስሜት ነው፡፡
በፖለቲካ ክርክሩ ጥርት ያለ አቋም ይዞ የመጣ የፖለቲካ ኃይል በምርጫ ውጤት የሚያገኘው ግን ሌላ ነው፡፡ በምርጫ 2002 ክርክር ማነው ያሸነፈው የሚለውን ለመለካት አንዳንድ ድርጅቶች ሞክረዋል፡፡ የእኛ ፓርቲ ኢዴፓ ትልቅ ውጤት ነው የነበረው፡፡ በምርጫው የተገኘው ውጤት ግን ተቃራኒ ነው፡፡ ሕዝቡ በዚህ ረገድ ብስለት ሊኖረው ይገባል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲመዝን በትምህርት ደረጃቸው፣ በአካባቢያዊ ማንነታቸው፣ በሀብት መጠናቸው፣ በዝናቸው መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ይዘውት በቀረቡት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ይኼን ከአሉባልታ፣ ከወሬና ከጥላቻ በፀዳ መልኩ መመዘን የሚችል ኅብረተሰብ መሆን አለበት፡፡ ኅብረተሰቡ ለዚህ ደረጃ ካልበቃ ብቁ የሆነ የፖለቲካ አመራር አያገኝም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ስህተቱ የእከሌ ነው ብለን ጣታችንን ወደ ሌላ ከመቀሰር ይልቅ፣ እኛም የችግሩ አካል ነን ብለን የመፍትሐው አካል ማድረግ ካልቻልንና አሁን በተያዘው አንዳችን የሌላችንን ኃጢያት እያጎላን በማውጣት ለአገሪቱ ችግሮች ሌሎችን ብቻ ተጠያቂ እያደረግን በመሄድ የትም ይደርሳል ብለን አናምንም፡፡ ይኼ አዲስ አስተሳሰብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የተቃዋሚው ጎራ ኢሕአዴግን ኢትዮጵያን ሊያጠፋ የሚሠራ አድርገው እንደሚስሉ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ኢሕአዴግ የሐሳብ ልዩነትን የማያስተናግድና ከሥልጣን መውረድ የማይፈልግ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጅት እንደሆነና የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት የማምጣት ፍላጎቱም እውነተኛ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ድምዳሜ ያደረሰዎት ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- በተቃዋሚው ጎራና የተቃዋሚው ደጋፊ በሆነው ኅብረተሰብ ዙሪያ ያለው አንዱ ችግርና ከዚህ እንዳይወጣ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ዋናው ጉዳይ፣ ኢሕአዴግ በገባ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ኢሕአዴግን ፀረ ኢትዮጵያዊ ኃይል አድርጎ ከቀረፀው አጀንዳ አለመውጣት ነው፡፡ ያኔ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመበታተን የመጣ ኃይል ነው በሚል ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ተሠርቶበታል፡፡ ያ ፕሮፓጋንዳ በኅብረተሰቡ ውስጥ ቀላል ቦታ አይደለም ያገኘው፡፡ በአንድ ወቅት የዚህ አስተሳሰብ ሰለባ እንደነበርኩ መጽሐፌ ላይ ገልጨዋለሁ፡፡ ትግል ውስጥ ገብቼ ነገሮችን በደንብ ከተጨባጭ እውነታ ጋር ለማየት ባደረግኩት ሙከራ ይኼ በጣም የተሳሳተ አቋም እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ችግሩ ያ አጀንዳ ዛሬም መለወጥ አልቻለም፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ 24 ዓመታት ቆይቶ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ሠርቶ በተለይ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በትምህርት፣ በጤና ቀላል የማይባሉ ነገሮችን ሠርቶም ይኼን አጀንዳ መለወጥ አልተቻለም፡፡ ይኼ አጀንዳ ትክክል አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ አምባገነናዊ ፓርቲ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣኑ በጣም ቀናኢ የሆነ ነው፡፡ ነገር ግን አቅሙና ሁኔታው በፈቀደለት መጠን በልማት ረገድ ይህችን አገር ለማሳደግ የሚጥር ነው፡፡ እርግጥ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ባህርይ የሌለውና ሥልጣኑን የማጋራት ፍላጎት የሌለው ፓርቲ ነው፡፡ በልማትና በማኅበራዊ ጉዳዮች ግን የብዙ ሚሊዮኖችን ችግር የፈታ መፍትሔ ያመጣ ፓርቲ ነው፡፡ ይኼን አቋም ሌሎች ፓርቲዎች ሊይዙት አልቻሉም፡፡ አሁን መንገድ ሲሠራ፣ መብራት ሲስፋፋ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ሲስፋፉ እየታየ አሁንም ለሕዝቡና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይኼን መንግሥት አገር እያፈረሰ ነው ብሎ መክሰስ እርስ በርስ የሚጋጭና የፖለቲካ ራስን ማጥፋት ነው፡፡ ይህን በማለት ኢሕአዴግን ሳይሆን የምትጎዳው የራስህን ተዓማኒነት ነው፡፡ ይኼን አመለካከት አለመቀበል ነው አንዱ ተቃዋሚውን ጎራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ሳይሆን እየተዳከመ እንዲሄድ ያደረገው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢሕአዴግን ርዕዮተ ዓለም እንዴት ያዩታል?
አቶ ልደቱ፡- ኢሕአዴግ የጠራ ርዕዮተ ዓለም አለው ብዬ አላምንም፡፡ ሲፈልግ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ይላል፡፡ በእውነት ልማታዊ መንግሥት ምን ማለት ነው የሚለውንም የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ እኔ ‘ዴቨሎፕመንት ስተዲስ’ ነው ያጠናሁት፡፡ በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት ልማታዊ ያልሆነ መንግሥት አለ ወይ የሚለውም አከራካሪ ነው፡፡ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ዴሞክራሲ ሳይኖራቸው ዕድገት ማምጣት ችለዋል፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ ጸሐፊዎች ልማታዊ መንግሥት ብለው የጠሯቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ ልማታዊ መንግሥት ነን የሚሉ አገሮች ዴሞክራሲ የሌላቸው ናቸው፡፡ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፀረ-ዴሞክራሲ ሆኖ እንደ ሥርዓት መቀጠል አልተቻለም፡፡ ስለዚህ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት በዴሞክራሲ ስለማያምኑ የመረጡት እኛም ልማታዊ መንግሥት ነን የሚለውን ነው፡፡ ኢሕአዴግ እስከ ምርጫ 97 ድረስ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ብሎ አያውቅም፡፡ የዴሞክራሲ እጥረት ነበረበት፡፡ በልማት ረገድ ግን የተሻለ ሥራ እየሠራ ነበር፡፡ ስለዚህ ራሱን ከልማታዊ መንግሥት ጋር ማያያዝ ፈለገ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ ልማታዊ መንግሥት የሚለውን ስም የጀመሩት፡፡ ስለዚህ ይኼ ነገር በደንብ ታቅዶ፣ ታምኖበት፣ በቂ የሆነ ውይይት ተደርጎበት የተደረሰበት አይመስለኝም፡፡ ኢሕአዴጎች የዴሞክራሲያዊ አገሮች መገለጫ የሆኑትን ነገሮች በአግባቡ ሠርተው ዴሞክራት ነን ማለት አልቻሉም፡፡ ወይም ደግሞ ዴሞክራሲ ለዚህ አገር አሁን አያዋጣውም፣ የሚያስፈልገው ልማት ነው ብለው በድፍረት መውጣት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የተሻለ ሆኖ ያገኙት ልማታዊ መንግሥት የሚለውን ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት የዴሞክራሲ ችግር አለበት ሲባል ደግሞ እኛ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ነን ማለት ተጀመረ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ የርዕዮተ ዓለም መስመሩን ለመምረጥ ተቸግሯል፡፡ በአንድ በኩል ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው አምንበታለሁ ማለት ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመጀመሪያ የሚያስፈልገን ልማት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ብጥብጥ ሊያመጣና ቅራኔ ሊያባብስ ይችላል ብሎ የማመን ጉዳይ አለ፡፡ ለሚመጣው 30 እና 40 ዓመት ጠንካራ መድበለ ፓርቲ አያስፈልገንም፣ ይልቁንም አንድ ጠንካራ የሆነ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ነው የሚያስፈልገን ብሎ በውስጥም የማመን ሁኔታ ይታያል፡፡ ሙስናን ከታገልን፣ ዴሞክራሲንም ቢሆን አፍነን ልማት እስካመጣን ድረስ ለዚህ አገር ይበጃል ብለው ያምናሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ውስጣዊ እምነት ይዘህ ወደ መድረክ ስትወጣ ይዘኸው የምትወጣው አስተሳሰብ ብዙም የጠራ አይሆንም፡፡ ይኼን ውዥንብር ነው ኢሕአዴግ ውስጥ እያየሁ ያለሁት፡፡
ብዙዎቹ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ስለልማታዊ መንግሥት ሲያወሩ ታሪካዊ አመጣጡን፣ ስኬታማ የሆኑ አገሮች እነማን ናቸው የሚለውን የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ በጽንሰ ሐሳቡ ላይ አጥኚዎች አይስማሙም፡፡ ወጥ የሆነ ባህርይ ያለው ልማታዊ መንግሥት የሚባል ነገር እስካሁን በዓለም ላይ የለም፡፡ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ራሳቸው በውስጥና በአካባቢያዊ ሁኔታቸው በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው እምነት ከቻይና ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን እናሳድግ፣ ሕዝቡ ሀብት ንብረት ይጨብጥ፣ ከዚያ በኋላ የፖለቲካ ለውጥ እናደርጋለን የሚል ነው፡፡ ይኼን ማለት ግን በምዕራቡ ዓለም ሊያስከትል የሚችለውን ተቃውሞ በማወቅና የሚመጣውን ተፅዕኖ በመፍራት የማለባበስ ነገር ነው ያለው፡፡ ከልማትና ከዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ በመጀመርያ የሚያስፈልገው የትኛው ነው የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ አንድ ድርጅት የትኛውም ዓይነት እምነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ያን ጉዳይ ስትፈጽም የኅብረተሰቡን ተቀባይነት ማግኘት አለብህ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጃት መጀመርያ የኢኮኖሚ ለውጥ ነው፣ ፖለቲካው ቀጥሉ ይመጣል ካለ ይኼንኑ አጀንዳውን መድረክ ላይ አውጥቶ ተከራክሮ ሕዝቡን ማሳመን አለበት፡፡ ሕዝቡ ካመነበት ያ ሥርዓት የኢትዮጵያ መገለጫ ቢሆን ችግር የለውም፡፡ የልማቱን ጉዳይ ኢሕአዴጎች በአፋቸው እንደሚናገሩት በተግባርም ሊገልጹት ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ የዴሞክራሲውን ጉዳይ ግን በአፋቸው እንደሚናገሩት በተግባር ሲገልጹት አይታይም፡፡ ኢሕአዴግ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የአስመሳይነት ባህርይ አለው፡፡ ይኼ በልማቱም ረገድ ሊመጣ የሚችለውን ፍጥነትና ዕድገት ይገታል፡፡ ሕዝቡ በሙሉ ልቡ እምነት ኖሮት ሥርዓቱ የሚያራምደውን አቋም ለአገርና ለሕዝቡ የሚጠቅም ነው ብሎ እንዳይሳተፍ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ የልማታዊ መንግሥት ነገር ውይይት የሚያስፈልገው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ብሔራዊ መግባባት ባለመፈጠሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የፈጠራቸውን ተፅዕኖዎች ‘መድሎት’ በተሰኘው ሁለተኛው መጽሐፍዎ ላይ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ፓርቲዎ ብሔራዊ መግባባት ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል የሚል አቋም አለው፡፡ ኢሕአዴግ ብሔራዊ እርቅ የሚለውን የማይቀበል ሲሆን፣ ብሔራዊ መግባባትም በሒደት ተፈጥሯል የሚል መከራከሪያ አለው፡፡ ዋናው ልዩነታችሁ ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- ይኼ የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውን በግልጽ የመተንተን ሁኔታ አልነበረም፡፡ ሁለት ችግሮች ናቸው የነበሩት፡፡ በአንድ በኩል ኢሕአዴግ ጉዳዩን በጣም አቃሎና አራክሶ የማየት አዝማሚያ ነበረው፡፡ የብሔራዊ እርቅ ጥያቄ የተጣላ ስለሌለ አያስፈልግም ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ አገሪቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ሊፈታ የሚችል በመሆኑ ማንኛውም አካል በዚያው መሠረት ይፈቱለታል የሚል አዝማሚያ አለው፡፡ ሁለተኛው ችግር የሚታየው በታቃዋሚው ጎራ ነው፡፡ ተቃዋሚው ጎራ ደግሞ ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል ሲል አዲስ የሽግግር መንግሥት ነው የሚመኘው፡፡ አዲስ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ፣ አዲስ ሕገ መንግሥት ተረቆና አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ሥልጣን እንዲያዝ ነው የሚፈለገው፡፡ ይኼም ስህተት ነው፡፡ ኢዴፓ ሦስተኛ ምርጫ ነው ይዞ የመጣው፡፡ ጉዳዩን ማራከስም ትክክል አይደለም፡፡ የተጣላ የለም፣ የባልና ሚስት ጉዳይ አይደለም ብሎ በዚህ አገር ብሔራዊ እርቅ ወይም መግባባት እንዳይመጣ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ በተግባር ፖለቲካችን ውስጥ ያለው ቅራኔ ይኼን አይደለም የሚያሳየው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ቅራኔ፣ ውጥረትና ጥላቻ ነው የሚታየው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እናቋቁማለን ብለን ሕጋዊ የምስክር ወረቀት ወስደን የተቋቋምን ፓርቲዎች አንዳንድ ጊዜ መድረክ ላይ ስንቀርብ የምንተያየው እንደ ጠላት ነው፡፡ ይኼ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ እርቅ አያስፈልግም ብሎ ጉዳዩን ማራከስ ትክክል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ሁልጊዜም አዲስ የሽግግር መንግሥትና አዲስ ሕገ መንግሥት እየመሠረተችና እያረቀቀች መኖር የለባትም፡፡ ይኼ አሁን ያለውም ሥርዓት ለእኛ ሽግግር ሆኖ ሊያገለግለን ይችላል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልገናል፡፡ የሚያስፈልገን ሥልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት መሆን የለበትም፡፡ ዋናው የሚያስፈልገው ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ሁላችንም አንድ የጋራ አገር ያለን መሆኑን አውቀን፣ በመቻቻልና በሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ መሥራት እንድንችል ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የፖለቲካ ልዩነት ኖሮዋቸው ግን በአገራቸው ጉዳይ ላይ በጋራ ይሠራሉ፣ ይከባበራሉ፣ ይደማመጣሉ፡፡ ይኼ ነው አገራችን ውስጥ የጠፋው፡፡ ልዩነት ችግር አይደለም፡፡ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ እኛ አገር ግን ችግር አድርገነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ መጠፋፋት እየሄድን ነው፡፡ ይኼን ማስቆም የሚችል መድረክ ይፈጠር ነው ያልነው፡፡ ይኼ ግልጽ ከሆነ ጉዳዩ ብሔራዊ እርቅ ወይም ብሔራዊ መግባባት መባሉ ለእኛ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን የነበርንበት አዙሪት መቆም አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በዘርና በሃይማኖት ያለው ውጥረት አልፎ አልፎ እንቅልፍ እንደሚነሳዎት መጽሐፍዎ ላይ ገልጸዋል፡፡ ከዚያም አልፈው የሩዋንዳው ዓይነት ጭፍጨፋ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይደገምበት ምክንያት እንደሌለም አመልከተዋል፡፡ አሁን አገሪቱ በሰላምና በመረጋጋት ትታወቃለች፡፡ በምን ምክንያት ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት? ከዚህስ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት?
አቶ ልደቱ፡- ወደዚህ ድምዳሜ ያደረሰኝ የፖለቲካ ሒደቱ ውስጥ ገብቼ ያየሁት ቅራኔ፣ ውጥረትና በመካከለችን ያለው ጥላቻ ነው፡፡ ይኼ በጣም አመቺ የሆነ ሁኔታ አንድ ወቅት ከፈጠረው ወደ ሩዋንዳው ዓይነት ሁኔታ አይወስደንም ብዬ ለማለት አልችልም፡፡ በተለይ በምርጫዎች አካባቢ በተለያዩ የፖለቲካ አጋጣሚዎች ያየናቸው ሁኔታዎች አስፈሪዎች ነበሩ፡፡ አሁንም ቢሆን አንዱ ሌላውን የሚያይበት መንገድና አንዱ ለሌላው የሚመኝለትን ነገር ካየህ ቅራኔው ቀላል አይደለም፡፡ አንዳንዱ ጉልበት ስለሌለው ነው እንጂ ጠብመንጃ በእጁ ቢገባ ብዙ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል የሚታይ ነው፡፡ ይኼ ጉዳይ ደግሞ በየጊዜው እየፈነዳ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታያል፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ብዙ ሕዝብ የሞተባቸው ግጭቶችን አይተናል፡፡ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የብዙ ሰዎች ሕይወት የጠፋባቸው ግጭቶችን አይተናል፡፡ እንደኔ እምነት እነዚህ ግጭቶች አሁን ደብዝዘው ነው የሚታዩት፡፡ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ የምናየው ኢሕአዴግ በፀጥታ ኃይሉ በከፍተኛ ደረጃ ጠንካራ ድርጅት በመሆኑ ነው እንጂ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የመቻቻል መንፈስና ባህል በመስፈኑ አይደለም፡፡ በእመቃ፣ በኃይልና በጉልበት የመጣ አንፃራዊ ሰላም ነው፡፡ ይኼን ጉልበት ኢሕአዴግ ዘለዓለም ይዞት ሊቀጥል አይችልም፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ይኼ ጉልበት የሚሟሽሽበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ እነዚህ ቅራኔዎች ጎልተው ወጥተው የአገር አደጋ የማይሆኑበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ የፀጥታ ኃይል አስፈላጊ ቢሆንም ኢሕአዴግ መተማመን ያለበት ኅብረተሰቡ ውስጥ በሚፈጥረው ብሔራዊ መግባባትና በመቻቻል ፖለቲካ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም በዚች አገር ጉዳይ ተሳታፊና ተጠቃሚ ነኝ የሚል ስሜት ማምጣት አለበት፡፡ ይኼ ስሜት እስካልተፈጠረ ድረስ ይኼ የተዳፈነ ቅራኔ አንድ ወቅት ሊፈነዳ ይችላል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ መጽሐፌ ላይ እንደገለጽኩት ይኼ ሥጋቴ እውን እንዲሆን አልፈልግም፡፡ ከእኔ በተቃራኒ የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያ የሰላም አገር ናት፣ ሰላም ሆና ትቀጥላለች ይላሉ፡፡ የእነሱ ምኞት ነው እዚህ አገር እውን እንዲሆን የምፈልገው፡፡ ነገር ግን ራሴን መዋሸት አልፈልግም፡፡ የፖለቲካ ሒደቱ ውስጥ ቀጥተኛ ሆኖ እንዳለፈ ሰው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው ቅራኔ አገርን እስከማፍረስ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ ፈርሰዋል የምንላቸው አገሮች በአንድ ወቅት እንደኛው የተረጋጉ የሚመስሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በውስጥ መሠረታዊ ቅራኔያቸውን ስላልፈቱ ዞሮ ዞሮ እዚያ ችግር ውስጥ ነው የገቡት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀውስ ሲፈጠር የሚጠቁት የኅብረተሰብ ክፍሎችና ድርጅቶች በሃይማኖትና በዘር እየተለዩ ነበር፡፡ ይኼ አደጋ ነው፡፡ አለባብሰን ልናልፈው አይገባም፡፡
ሪፖርተር፡- በግልዎ በአሉባልታ መጠቃት የጀመሩት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ጎልቶ ብዙ ሰው ያወቀው ከምርጫ 97 በኋላ ነው፡፡ በቅንጅት ውስጥ እርስዎ በግልና ፓርቲዎ አዴፓ የነበረው ሚና አሁንም የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ አለመግባባቱ የተፈጠረው ለምንድን ነበር? ከዚያስ በኋላ ባለው እንቅስቃሴያችሁ ምን ያህል ተፅዕኖ ፈጥሮባችኋል? 
አቶ ልደቱ፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ደግመው ደጋግመው በመነገራቸው የገነኑ ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ይኼው የኅብረት ጥያቄ ነው፡፡ ማንም ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው መቼም ኅብረት እንደሚጠቅም አይጠፋውም፡፡ መተባበር የተሻለ ጥንካሬ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ ሒደት መተባበር በራሱ ግብ አይደለም፡፡ የራሳቸውን ድክመት መሸፈን የሚፈልጉና ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተው በቂ የሆነ የማንቃትና የማደራጀት ሥራ መሥራት ያልቻሉ የፖለቲካ ኃይሎች ሁልጊዜ የኅብረት ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ሕዝቡም ደግሞ ኅብረት ጥነካሬ ነው፣ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ብሎ በማሰብ ሁልጊዜም የኅብረት ጥያቄን በቅንነት ነው የሚያየው፡፡ ስለዚህ ግራ ቀኙን ሳያይ የኅብረት ጥያቄን ሁሉ ይደግፋል፡፡ ቅንጅት ይኼ ጫና የፈጠረው ኅብረት ነው፡፡ አባሎቹ ተመሳሳይ የፖለቲካ ግብ የነበራቸው አልነበሩም፡፡ ግን ይኼን ልዩነታቸውን ከማየት ይልቅ ግፊቱን ተቀብለዋል፡፡ ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ የሚለውን አጀንዳ ፕሬሱም በጣም ያጮኸው ነበር፡፡ ይኼን አስተሳሰብ መጠየቅ በሌላ የሚያስጠረጥርና ለአሉባልታ ሰለባ የሚያደርግ ነበር፡፡ ስለዚህ ያ ኃይል በውስጡ ችግሮች እያሉና ዓላማው የተለያየ መሆኑ እየታወቀ፣ ግፊቱን መቋቋም አቅቶት ወደ አንድነት መጥቷል፡፡ በግፊት መምጣቱ መሠረታዊ ችግር ነበር፡፡ እውነተኛ የሆነ ውይይት ተደርጎ፣ የጋራ አንድነት የሚያመጡ አጀንዳዎች በደንብ ተለይተው አይደለም ቅንጅት የተፈጠረው፡፡ መጽሐፉ ላይ እንዳየኸው የዚህ ኅብረት አባል መሆናችን ስህተት ነበር፡፡ እዚያ ውስጥ ከነበሩ አንዳንድ ኃይሎች ጋር መቼውንም ቢሆን አንድ ላይ መሥራት እንደማይቻል እናውቅ ነበር፡፡ እያወቅን ግን አብሮ ባለመሥራት ሊመጣብን የሚችለውን ጣጣና ጫና በመፍራት ውስጥ ሆነን እንታገላለን ብለን መሄዳችን ትልቅ ስህተት ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን ጉዳዩን በጥልቀት የመረመሩትም ሰዎች ጭምር ኢዴፓ ለመለያየት የወሰነበት ጊዜ ተገቢነት ላይ ጥያቄ አላቸው፡፡ በውጥረት መካከል እያለ ከምትወጡ የምታውቁት ችግር እስከሆነ ድረስ መታገስ ነበረባችሁ በማለት ለሚተቿችሁ ምን ምላሽ አላችሁ?
አቶ ልደቱ፡- በመጽሐፌ ላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት እኛ አልወጣንም፡፡ ተገፍተን ነው የወጣነው፡፡ አንዳንድ ሰው እኛ አንፈልግም በቃን ብለን እንደወጣን ነው የሚያስበው፡፡ ነገር ግን እኛ እስከ መጨረሻው ድረስ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ነው የሄድነው፡፡ እሱ ሳይቻል ሲቀር ነው የወጣነው፡፡ የወጣነውም ደግሞ ተባረን ነው፡፡ የመነጣጠሉ የመጨረሻ መጀመሪያ የሆነው የእኔና የአቶ ሙሼ ሰሙ ከቅንጅት ተባረዋል መባል ነው፡፡ እኛን የወከለን ኢዴፓ ነው፡፡ ከዚያ ሊያወጣንም ከፈለገ ማውጣት ያለበት ኢዴፓ ነው፡፡ ቅንጅት የሚባል አባል የሆንበትና ሊያባርረን የሚችል ድርጅት አልነበረም፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ ከስምምነታችን ውጪ አባርሬያቸዋለሁ አለ፡፡ የእሱ ተወካዮች በተባረሩበት ሁኔታ ኢዴፓ ሊቀጥል አይችልም፡፡ በተፈጥሮው ቅንጅት በዴሞክራሲ አግባብ ችግሮችን የመፍታት ባህል ስላልነበረው በአሉባልታ አሸማቆ ሐሳቡን በኃይል ለመጫንና እንድንቀበለው ለማድረግ ነው የሞከረው፡፡ ስለዚህ ጊዜውን እኛ አልመረጥንም፡፡ ለውጡንም ከመንግሥት ለውጥ አንፃር ብቻ ነበር ያዩት፡፡ እኛ ደግሞ ከዚያ በመለስ ያሉትን ውጤቶች መጠበቅ አለብን አልን፡፡ ሥልጣን ካልያዝን ሌላውን አንቀበልም አሉ፡፡ ወደ ፓርላማ እንግባ አንግባ ሲባል የኢዴፓ አቋም ያለንን ይዘን በዚያ ላይ እየደመርን እንሂድ የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ መለያየቱ ተፈጥሯዊ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግና አቶ መለስ ዜናዊ በሚነፃፀሩበት ሁኔታ አቶ ልደቱና ኢዴፓን ለመለየት የሚቸገሩ አሉ፡፡ ኢዴፓ አቶ ልደቱን ቀረፀ ወይስ አቶ ልደቱ ኢዴፓን ቀረፁ?
አቶ ልደቱ፡- ማንኛውም ሐሳብ ከአንድ ሰው ነው የሚጀምረው፡፡ በሒደት በውይይት እየዳበረ ነው ያ ሐሳብ የብዙዎች አስተሳሰብ የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ኢዴፓ ውስጥ ያለው እውነታ የተለየ ነው፡፡ የኢዴፓ መሠረታዊ አስተሳሰብ የተፈጠረው በ1992 ዓ.ም. ነው፡፡ ኢዴፓን ስናቋቁም የትግላችንን አቅጣጫ ለይተን ነበር፡፡ ገዥውን ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ኅብረተሰቡን እንዴት እንዋጋው የሚለው የተለየው ያኔ ነው፡፡ ወደዚህ አስተሳሰብ ለመድረስ የአንድ ዓመት ሙሉ ውይይት ነው ያደረግነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ሚና ሊኖረኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሌሎች ግብዓት ሳይጨመር የፓርቲው አቋም የሆነ ጉዳይ የለም፡፡ በብዙ የክርክር መድረኮች የምቀርበው እኔ ስለነበርኩ ብዙዎች በእኔና በፓርቲው መካከል ልዩነት እንዳይፈጥሩ አድርጓል፡፡ ይኼ ስህተት ነው ብለን በማመናችን እሱን በሒደት ለውጠናል፡፡ አሁን እኔ አመራር ውስጥ የለሁም፡፡ አንዳንዶች ግን ያ አስተሳሰብ አሁንም አላቸው፡፡
ሪፖርተር፡- አሉባልታዎቹ ከፓርቲዎ ይልቅ እርስዎ ላይ በጣም ያነጣጠሩ እንደነበሩ በመጽሐፍዎ ላይ በዝርዝር ጠቅሰዋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይህ ጉዳይ ፓርቲውን እንዳይጎዳ በማሰብ የተወሰኑ የኢዴፓ አባላት እርስዎ ከጀርባ ሆነው እንዲሠሩ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ልደቱ፡- ፓርቲው ውስጥ ያለው እውነታ ተቃራኒ ነው፡፡ ራሴን ከአመራሩ ለማውጣት መጣር የጀመርኩት ከ12 ዓመት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ እንባ አውጥቼ ለመውረድ ጠይቄ እምቢ ተብዬ የገባሁበት ጊዜ አለ፡፡ የእኔ ሚና መቀነስ እንዳለበት የጠየቅሁት እኔ ነኝ፡፡ ሌሎቹ እንዲያውም አሉባልታ ፈርተህ ነው ወይ እንዲህ የምትለው ብለው ተቃውመዋል፡፡ አንድም መድረክ ላይ በሚወራብህ አሉባልታ ፓርቲውን እንዳትጎዳ ከአመራር ውረድ ሲባል አይቼ አላውቅም፡፡
ሪፖርተር፡- ከ20 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ዘልቀዋል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የተቃዋሚው ጎራ የህልውና ጥያቄ እየተነሳበት ባለበት ጊዜ በምርጫው ዕጩ ሆነው አለመቅረብዎ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ የምርጫ 2002 ውጤት ካደረሰብዎ ጉዳት እስካሁንም አለማገገምዎና በሥርዓቱ ተስፋ ለመቁረጥዎ ማሳያ ተደርጎም እየቀረበ ነው፡፡ ላለመሳተፍ ለምን ወሰኑ? ወደፊትስ ዕቅድዎ ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- አንድ ሰው በምርጫ ሲሸነፍ ተስፋ የሚቆርጥ ከሆነ ትክክል አይደለም፡፡ ከ12 ዓመት በፊትም ተሸንፌ ነበር፡፡ በ1992 ዓ.ም. ኢዴፓ ለፓርላማና ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ተወዳድሮ አሸንፏል፡፡ ያኔ እኔ አልተወዳደርኩም፡፡ ዘመቻውን የመራሁት እኔ ነበርኩ፡፡ በክርክሮች ላይ የምቀርበው እኔ ነበርኩ፡፡ ግን ዕጩ አልነበርኩም፡፡ ሚናህን እንደተጨባጩ ሁኔታ ልትመርጥ ትችላለህ፡፡ የግድ ተወዳዳሪ ሆነህ መቅረብ የለብህም፡፡ እኔ እንዲያውም ለቀበሌ ተወዳድሬ ነው የተሸነፍኩት፡፡ ለቀበሌና ለወረዳ ምርጫ ሰዎች ብዙ ትኩረት ስለማይሰጡት የመጀመርያ ተሳትፎዬ ለቀበሌ ምክር ቤት ነበር፡፡ ሌላው የደረሰብኝ ጫና ተስፋ ለመቁረጥ ምክንያት ቢሆን ኖሮ ከ97 በኋላ ነበር ማቆም ያለብኝ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የፓርቲው ሊቀመንበር እንድሆን ቅስቀሳ አድርጌ የተመረጥኩት ከ97 በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት እየተለመንኩ ነበር የምመረጠው፡፡ ከ97 በኋላ ግን ፓርቲው ችግር ውስጥ ወድቆ ጥየው ልሄድና ተስፋ ልቆርጥ አልችልም ነው ያልኩት፡፡ በምርጫ ማሸነፍና መሸነፍ ያለ ነገር ነው፡፡ መሸነፍ አልነበረብኝም ካልኩ ፖለቲካ አልገባኝም ማለት ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ሆነህ ስታስበው ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ለትግሉ የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለብኝ ነው ያስተማሩኝ፡፡ ትግሉ ገና ብዙ ድካምና መስዋዕትነት እንደሚጠይቅ ነው ያሳዩኝ፡፡ ወደፊትም በምንም ሁኔታ ወደኋላ አልልም፡፡ ያ ማለት አንዳንዴ ለግል ጉዳይህ ቅድሚያ አትሰጥም ማለት አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment