በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈለጋቸው ተገለፀ። መንግስት ብሔራዊ ሰብአዊ ፍላጐት እና ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን ሁኔታ በማገናዘብ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ ጉዳይ አስተባባሪ ቢሮ እንዳመለከተው በዚሁ በፈረንጆቹ ዓመት ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። አስቸኳይ የምግብ እርዳታው ከሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በኦሮሚያ ክልል እንደሚገኙም መረጃው አስቀምጧል። በዚህም መሠረት 38 በመቶዎቹ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ሲሆኑ፤ 31 በመቶዎቹ በሶማሌ ክልል፣ 12 በመቶዎቹ በትግራይ ክልል እንዲሁም 6 በመቶዎቹ በአማራ ክልል እንደሚገኙ ተገልጿል። የእርዳታ ተልዕኮው በስነ-ምግብ፣ በጤና፣ በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ በግብርና እና በትምህርት ዘርፍም እርዳታ ማድረግ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለማገዝ ታቅዷል። ይህን ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ሰብአዊ እርዳታ ለማከናወንም 386 ሚሊየን ዶላር ገደማ እንደሚጠይቅ ነው የተገለፀው። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ እ.ኤ.አ ከ2014 የተሸጋገረ 41 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንዳለ እና የሚያስፈልገውን ያህል ገንዘብ የማግኘት እድሉም ይሄን ያህል ተስፋ የሚጣልበት እንዳልሆነ ተገልጿል። ለጋሾችም በዚህኛው ዓመት እርዳታውን ለማድረግ እያሳዩ ያሉት ተነሳሽነት መቀነስ አሳይቷል ብሏል ዘገባው።
No comments:
Post a Comment