Tuesday, March 17, 2015

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ‹‹መብቴን ካላከበርክ እኔም….. !›› ወደሚልበት የትግል ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገለፀ!

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ‹‹መብቴን ካላከበርክ እኔም….. !›› ወደሚልበት የትግል ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገለፀ!
ለ 3 አመታት በተለያዩ የሰላማዊ ትግል ዘዴዎች መብቴን አክብሩ ሲል የቆየው ህዝበ ሙስሊም የህዝብን ድምፅ ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆነው የሃገራችን መንግስት በቀጣይ የህዝብን ድምፅ ይሰማ ዘንድ ወደሚያስገድዱ ህዝባዊ እንቢተኝነት ትግሉ መሸጋገሩን ድምፃችን ይሰማ አስታውቋል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ‹‹መብቴን ካላከበርክ እኔም….. !›› ወደሚልበት የትግል ምዕራፍ ላይ እነሆ ደርሰናል!
ሰኞ መጋቢት 7/2007
ሕዝብ የአንድ አገር መሠረት ነው፡፡ የአገር ምሰሶዎች የሚተከሉትም በህዝብ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ሕዝብ ለአንድ አገር ሕልውና ዋነኛው ምንጭ ነው›› ብንል በእርግጥም አንሳሳትም፡፡ የመንግስት ተቋማትም ሆነ መንግስት ራሱ የመቋቋሚያ ዓላማው ህዝብን ማገልገል፣ የህዝብን ፍላጎት ማስፈጸም ነው፡፡ ይህ ሳይሆንለት ሲቀር ህዝብ ይቀየማል፤ ይቆጣልም፡፡ መብቱን በተለያዩ መንገዶች መጠየቅ ይጀምራል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሙስሊምም ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲያደርግ የቆየው ይህንኑ ነው፡፡
ትግል የራሱ ደረጃዎች ያሉት ሂደት ነው፡፡ በለዘብተኛ አቤቱታ ይጀምራል፡፡ ድርድሮችን ያልፋል፡፡ ጠንከር ያሉ የመብት ጥየቃ ሂደቶችን ያሳልፋል፡፡ ጥያቄውም ወደትግል ይቀየራል፡፡ መስዋእትነቶች ይከፈሉበታል፡፡ እያዳንዷ መስዋእትነት በራሷ ለትግሉ የሚኖረ-
ውን ቁርጠኝነት እና ወኔ እየጨመረች ትሄዳለች፡፡ አሁንም ችግሩ ካልተፈታ ህዝብ ያገለግለው ዘንድ ራሱ በሾመው አካል ላይ ተስፋ መቁረጥ ይጀምራል፡፡ የአገሪቱ ተቋማት ዋነኛ ባህሪያቸውን ለውጠው በደልን የማገልገል ሚና መወጣት በቀጠሉ ቁጥር የህዝቡም ቁርጠኝነት በዚያው ልክ እያደገ ይመጣል፡፡
የአንድ መንግስት ህልውና በእሺተኛ ህዝብ ፍቃደኝነት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ሕዝብ ሲመረውም ‹‹መብቴ ይከበርልኝ›› ከሚል ጩኸት ‹‹መብቴን ካላከበርክ እኔም….. !›› ወደሚል ዛቻ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህን ጊዜ ሕዝቡ ‹‹ትብብር የመንፈግ ትግል ውስጥ ገባ›› ይባላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ትግል ውጤታማ መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን አጽንኦት ሰጥተው ያስተምራሉ፡፡
አዎን! በጨዋ ደንብ እና በአንጸባራቂ ሰላማዊ ስነ ምግባር ለሶስት ዓመታት መብቱን ሲጠይቅ እና ሲታገል የቆየው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ‹‹መብቴ ይከበርልኝ›› ከሚል ያልተሰማ ጥያቄው ‹‹መብቴን ካላከበርክ እኔም….. !›› ወደሚልበት የትግል ምዕራፍ ላይ እነሆ ደርሰናል! ሰሞኑን ይህንኑ አስመልክቶ የምንለው ይኖራልና ሁላችንም ቃል የገባንበትን ትግል እስከድል ደጃፎች ለማድረስ ወገባችንን እናጥብቅ፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
997064_462370593912631_8224303692591003294_n

No comments:

Post a Comment