Saturday, June 27, 2015

እነ ወይንሸት ሞላ አዲስ ክስ ቀረበባቸው

                                                                            መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ እስር ላይ ቆይተው እንዲፈቱ ተወስኖላቸው ከእስር ቤት ሲወጡ
እንደገና በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት ወንይሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤትሄልየም አካለወርቅ ላይ ፖሊስ
አዲስ ክስ አቀረበ፡፡
እነ ወይንሸት ሰኔ 18/2007 ዓ.ም ቀደም ብለው ተከሰውበት በነበረው ተመሳሳይ ‹ወንጀል› ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ይዞ
ቀደም ብለው ውሳኔ ባገኙበት በተመሳሳይ ቄራ ፍርድ ቤት ቀርበው ዳኞቹ ‹‹እኛ ፈርደናል፤ እንዲለቀቁም ወስነናል፣ ከዚህ
በኋላ ይህን ጉዳይ አናይም›› በሚል መዝገቡን እንደማያዩ ገልጸው መመለሳቸው ይታወቃል፡፡
ይሁንና ዛሬ ሰኔ 19/2007 ዓ.ም በቄራ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ ‹‹ምስክሮችና የምስክሮቹ ጓደኞች ላይ ዛቻና
ማስፈራሪያ አድርሰውብኛል›› ሲል ሌላ ክስ አቅርቧል፡፡ ፖሊስ እነ ወይንሸት ሰኔ 15/2007 ዓ.ም በቄራ ፍርድ ቤት በዋለው
ችሎት ቀርበው እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው በኋላ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ የነበሩትን ምስክሮችና የምስክሮች ጓደኞችን ‹‹ወያኔ
ለዘላለም አይኖርም፣ እንገናኛለን፣ ቤታችሁን እናውቀዋለን፣ የወያኔ ተላላኪዎች›› በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ አድርሰውብኛል ብሏል፡፡
ሆኖም እነ ወይንሸት በወቅቱ የመሰከሩባቸውን ሰዎች ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ እንዳላዩዋቸው፣ ዛቻና ማስፈራሪያም
እንዳላደረሱባቸውና ክሱ ሆን ተብሎ እስር ላይ ለማቆየት የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
እነ ወይንሸት በአዲሱ ክስም የዋስትና መብት የተከለከሉ ሲሆን በምስክሮችና የምስክሮች ጓደኞች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ
አድርሰውብኛል ያለው ፖሊስ ምስክር ለማሰማት ለማክሰኞ ሰኔ  23/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡

No comments:

Post a Comment