
የአልበሽር ጉዳይ ሰሞኑን ፌስቡክን ተቆጣጠራት፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ በርካታ አስተያየቶች ስለተሰጡ እኔ ብዙም የምጨምረው ላይኖር ይችላል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሱዳናውያን ምን ይላሉ በሚለው ነጥብ ዙሪያ ብዙም የተወራ ስላልመሰለኝ ያንን ለመነካካት ነው ሃሳቤ፡፡
…..…
…..…
ሁለት ሱዳናውያን ወዳጆች አሉኝ፡፡ አንደኛው በሐሰን ቱራቢ ዘመን በበጎ ፈቃድ ጅሃድ ለማካሄድ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ሁለት ጊዜ ወደ ደቡብ ሱዳን ዘምቷል፡፡ አሁን አሁን የኡመር አልበሽር መንግሥት እውነተኛ እስላማዊ መንግሥት አይደለም የሚል አቋም ስለያዘ ከፓርቲው ርቋል፡፡ ሁለተኛው ከተማሪነቱ ዘመን ጀምሮ እስላማዊ ነኝ በሚለው መንግሥት ሲታሰር ሲፈታ የቆየ፣ በተለያየ ጊዜ ብዙ አይነት ማስፈራሪያና ቶርቸር ደርሶበትም ከአቋሙ ንቅንቅ ያላለ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ነው፡፡
ደስ የሚለው ነገር ሁለቱም በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የአንድ ቡድን አባላት መሆናቸው ነው፡፡ ስለ ሕይወት፣ ስለ አገራቸው ፖለቲካ፣ ስለ ሃይማኖት… የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም አብረው ይሠራሉ፣ ሻይ ቡና ይገባበዛሉ፡፡ አልፎ አልፎም ክርክር ቢጤ ያደርጋሉ፡፡
አንድ ቀን በጆርጅ ቡሽ ዙሪያ መወያየት ጀመሩ፡፡ ‘ሰውየው ደንቆሮ ቢጤ ነው’ በሚለው ላይ ተስማምተው ሲሳሳቁ ቆዩ፡፡ ቀጥሎ ተቃዋሚው የተለየ ሃሳብ አመጣ፡፡
“ከኡመር አልበሽር አይነት ደንቆሮ ግን ጆርጅ ቡሽ ይሻለኛል”
“እንዴት?”
“አሜሪካኖች እንዲያ ያለ ደንቆሮ ሲያጋጥማቸው ከቻሉ በአራት ዓመቱ ያሰናብቱታል፤ ያ ባይሳካ ደግሞ ከስምንት ዓመት በኋላ የስልጣን ዘመኑ ሲያበቃ የግድ በሌላ ፕሬዚደንት ይተካል፡፡ እኛ ግን ይኸው በአንድ ሰው ከሃያ ዓመት በላይ እየተገዛን ነው፡፡ እና የጆርጅ ቡሽ ድንቁርና ይሻላል፡፡”
በዚህ ጊዜ ጓደኛው ተበሳጨ፡፡ የክርክራቸውን የመጨረሻ ቃል ተናገረ….
“እንዴት ኡመር አልበሽርን ከአንድ ካፊር ጋር ታወዳድራለህ!?”
….
እና ሱዳን ውስጥ የኡመር አልበሽር ደጋፊም ተቃዋሚም አለ፡፡ ‘የሱዳን ሕዝብ ተደፈረ’ ብለው የሚያወሩ ሰዎች ያላወቁት ይህን ይመስለኛል፡፡
….
እና ሱዳን ውስጥ የኡመር አልበሽር ደጋፊም ተቃዋሚም አለ፡፡ ‘የሱዳን ሕዝብ ተደፈረ’ ብለው የሚያወሩ ሰዎች ያላወቁት ይህን ይመስለኛል፡፡
በኡመር አልበሽር ላይ የእስር ትዕዛዙ በወጣበት ዕለት እኔ ከሱዳን ውጭ ሌላ ሃገር ነበርኩ፡፡ ስብሰባ ላይ እያለሁ አንድ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ “አልበሽር አበቃለት!” የሚል፣ ደስታን ለመግለጽ ፈገግ ያለ ፊት የታከለበት ነበር፡፡
በነገራችን ላይ በትዊተርና በአቫዝ “አልበሽርን እሰሩልን” የሚል ዘመቻ ተጀምሯል፡፡ የጀመሩት ደግሞ ሱዳናውያን ናቸው፡፡
…
በሌላ በኩል ደግሞ የICC ድርጊት የውጭ ተፅዕኖ መገለጫ ነው የምንል ሰዎች መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ አለ፡፡ በየሃገሮቻችን ውስጥ ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ብናሰፍን ማንም መጥቶ እጃችንን ለመጠምዘዝ የሚችልበት ብዙ ክፍተት ሊኖር እንደማይችል አንርሳ፡፡
…
በሌላ በኩል ደግሞ የICC ድርጊት የውጭ ተፅዕኖ መገለጫ ነው የምንል ሰዎች መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ አለ፡፡ በየሃገሮቻችን ውስጥ ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ብናሰፍን ማንም መጥቶ እጃችንን ለመጠምዘዝ የሚችልበት ብዙ ክፍተት ሊኖር እንደማይችል አንርሳ፡፡
መልካም ቀን
No comments:
Post a Comment