Wednesday, June 17, 2015


ጴትሮስ አሸናፊ
በቅዱስ መጽሐፍ በአለማችን ረጅሙን እድሜ ማቱሳላ( 969 ዓመት )መኖሩን አንብበናል። (ዘፍ 5፣27) ከዚያም ለጥፋት ውሃ ምክንያት በሆነው የሰው ኃጢአት ምክንያት 120 መድረሱን ብናነብም ይስሐቅ 180 ዓመት መኖር ችሏል። ከዚያም ወርዶ 70 ከበዛም 80 ዓመት ሲሆን ይህንን ካለፈ ትርፉ ድካምና መከራ እንደሆነ ነግሮናል።
«የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና» መዝ 90፣10
ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ የጆሀንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንድ ወንጀለኛ ላይ ያሳለፈበት የ1535 አመት የእስር ውሳኔ ፍርድ የሚያስገርምና የሰው ልጅ እድሜ ቢበዛ ስንት ሆኖ ነው ይሄን ያህል አመት የተፈረደበት የሚል ጥያቄ የሚጭር ነው።
አልበርት ሞራኬ ይባላል ። የ35 አመት ጎልማሳ ነው። በምስራቃዊ ጆሃንስበርግ አይቮሪ ፓርክ ነዋሪ ነው።
በ175 የተለያዩ የወንጀል ክሶች ፍርድ ቤት ቀርቦ በ144 ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሏል ።
የተከሰሰባቸውን ወንጀሎች የተመለከትን እንደሆነ
* 30 የአስገድዶ መድፈር
* 41 የአፈና
* 24 የዘረፋና ሌሎች ተደራራቢ
* 3 የዘረፋ ሙከራ
* 1 የመግደል ሙከራ
እንዲሁም የጦር መሣሪያ ያለፈቃድ መያዝና ሌሎችም ወንጀሎች ናቸው ።
የጆሀንስበርግ ችሎት ያሳለፈበት የ1535 አመታት እስራት ሲተነትን እንደሚከተለው ይሆናል:
* በተደጋጋሚ ለመፈፀማቸው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የ30 አመት ፅኑ እስራት፣
* በዘረፋ ወንጀል በቀረቡበት ክሶች በያንዳንዱ 15 አመት እስራት፣
* በመግደል ሙከራ 10 አመት እስራት፣
* በአፈና በቀረቡበት ክሶች በያንዳንዱ 5 አመት እስራት፣
* በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በመያዝ 5 አመት እስራት
ጎልማሳው አልበርት ሞራኬ በተከሰሰባቸው 175 ክሶች በሙሉ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ የተከራከረ ቢሆንም በአስገድዶ መድፈር ከቀረቡበት 30 ክሶች ብቻ በ29 ጥፋተኛ ሆኖ ከመገኘቱም በተጨማሪ በአጠቃላይ በ144 ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆኑን የመሐል ዳኛው ሪያን ስትሪደም ይናገራሉ ።
ከአስገድዶ መድፈር ሰለባዎቹ አንዷ ኪቤትስዌ ማዋሻ ላለፉት 2 አመታት የልደት ቀኗን እየጠበቀ 2 ጊዜ እንደደፈራትና ልደቷን ማክበር እንዳልቻለች ተናግራ አሁን ግን አልበርት ሞራኬ በመታሰሩ የፊታችን ሜይ 7ቀን 29ኛ አመት ልደቴን በሰላም አከብራለሁ ብላለች ( ሌላ እንዳያጋጥማቸው እየፀለይን) ።
ችሎቱን የመሩት ዳኛ ሪያን ስትሪደም ስለ ሞራኬ ሲናገሩ
“ሞራኬ በፈፀማቸው ወንጀሎች የማይፀፀት ከመሆኑም በላይ አንድም ወንጀል እንዳልፈፀመ አስረግጦ ሲናገር እንኳ ሃፍረት አይሰማውም ከዚያም አልፎ የአስገድዶ መደፈር ሰለባዎቹን ለወደፊቱ ራሳቸውን እንዴት ከጥቃት መከላከል እንደሚችሉ ለመምከር ይሞክራል ” ይላሉ።
የሞራኬ የ1535 አመት እስር በደቡብ አፍሪካ ክብረወሰን ነው ወይ ቢባል በፋፁም አይደለም። እኤአ በ2007 ዓ/ም ሞንጌዚ ጂንዜላ የተባለ የ39 አመት ጎልማሳም በ60 የአስገድዶ መድፈርና ተያያዥ ወንጀሎች ተከሶ የ55 አመት ፅኑ እስራትን ጨምሮ የ2461 አመት እስር ተፈርዶበታል።
እኤአ በ2013 ዓ/ም ምሉንጊሳ ምሻሊ የተባለ ሌላ ወንጀለኛ ደግሞ በ39 አስገድዶ መድፈር ክስ የ39 አመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል ።(አላነሰችም? )
ሞራኬ አሁን የ35 አመት ጎልማሳ ሲሆን የ1535 አመት እስሩን ሲጨርስ የ1570 አመት አዛውንት ይሆናል ማለት ነው። የሞራኬ የሙያ አጋር የ39 አመቱ ሞንጌዚ ጂንዜላ ደግሞ የ2461 አመት እስሩን ሲጨርስ የ2500 አመት የእድሜ ባለጸጋ ይሆናል ማለት ነው። ከሁለት ሚሊኒየም በላይ።
…………………………………….
ፎቶው የ35 አመቱ ሞራኬ ነው
ጴትሮስ አሸናፊ

No comments:

Post a Comment