
የአንድነት ፓርቲ አባል እና የሚሊየኖች ድምፅ አምደኛ የነበረው እስማኤል ዳውድ ትላንትና ከጠዋቱ ሁለት ሰአት ሲቪል በለበሱ ሰዎች ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዶ ለእስር መዳረጉን ወላጅ እናቱ አስታወቁ፡፡
እስማኤል፣ ከጠዋቱ ሁለት ሰአት ሲቪል የለበሱ ሰዎች ቤቱ በመምጣት ‹‹ቃል ሰጥተህ ትመለሰላህ›› በማለት ከቤቱ ወደ አራዳ ፖሊስ ጣቢያ ከወሰዱት በኋላ ‹‹ቃሉን ሰጥቶም ቢሆን መለቀቅም እንደማይችል አስታውቀውት ወደ ወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ መዘዋወሩን›› ወላጅ እናቱ ገልፀዋል። በትላንትናው እለትም ከአራዳ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ ተደውሎላቸው ችሎት መድሃኒያለም አካባቢ ወደሚገኘው ወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ መዘዋወሩን እንደተገለፀላቸው አስረድተዋል።
እስማኤል፣ በዛሬው እለት ፒያሳ በሚገኘው አራዳ ፍርድ ቤት ከረፋዱ 5፡30 የቀረበ ሲሆን በችሎቱ የተሰየመችው ዳኛ ‹‹በአራት ቀን ውስጥ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ለክስ የሚያበቃ በቂ ማስረጃ ካለው ፍርድቤት እንዲያቀርበው አለበለዚያ ግን በነጻ እንዲያሰናብተው›› ትእዛዝ አስተላልፋለች፡፡ ወላጅ እናቱን በምን ምክንያት ለእስር እንደተዳረገ ላነሳሁላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ከረቡዕ ሰልፋ ላይ በመገኘቱ ምክንያት እንደሆነና ከእሱም ሌላ ሁለት ጓደኞቹ ለእስር መዳረጋቸውን›› ገልፀዋል፡፡
ፖሊስ በረቡዕ ሰልፍ ላይ ተገኝተው ተቃውሟቸውን በመንግስት ላይ የገለፁ ወጣቶችን ከቤታቸው እያደነ በማሰር ላይ እንደሚገኝ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ መንግስት በበኩሉ በረቡዕ ሰላማዊ ሰልፋ ላይ ለተነሳው ግጭት ሰማያዊ ፓርቲና ህገ-ወጥ ሲል የሰየመውንና በቀድሞ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ ይመራ የነበረውን የአንድነት ፓርቲ አባላትነትን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ስድስት አባሎቹ እንደታሰሩ ያስታወቀ ሲሆን ‹‹ህገ-ወጡ›› አንድነት በመባል በመንግስት የሚጠራውና በቀድሞ የፓርቲው ፕሬዝዳንት በላይ ፍቃዱ ይመራ ከነበረው አንድነት ውስጥ ለእስር የተዳረጉት ቁጥራቸው ሶስት ደርሷል፡፡ አቶ እስማኤል ዳውድ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና የፓርቂው የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ዳዊት አስራደ ከረቡዕ ሰልፋ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ እስማኤል ዳውድ፣ በትእግስቱ አወሉ በሚመራውና በበዙዎች ዘንድ ህገ-ወጡ አንድነት በመባል በሚታወቀው የፓርቲው አባላት አማካኝነት ስም የማጥፋት ክስ ተመስርቶበት ለሀያ ቀናት ታስሮ በዋስ መለቀቁ የሚታወስ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment