Friday, April 24, 2015

በስቶክሆልም የመድኃኒዓለም ቤ/ክ በሊቢያ ለተገደሉ ወገኖቻችን ጸሎት ምሕላ ተደረገ


Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. April 22, 2015)፡- ዛሬ ማምሻውን ከ12 ሰዓት (18፡00) ጀምሮ ለሁለት ሰዓታት በስቶክሆልም በደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በሊቢያ ለተገደሉት ወገኖቻችን በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የምስራቅ አፍሪካና የአውሮጳ ሊቀጳጳስ የተመራ ሥርዓተ ጸሎት ተደረገ። በርካቶች ሲያለቅሱ ነበር።
በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በግፍ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ሞት ያስደነገጣቸው ከ300 በላይ ምዕመናን የተገኙ ሲሆን፣ የእስልምና እምነት እና የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተከታዮች በአንድነት ተሰባስበው ተገኝተዋል።
በስቶክሆልም መድኃኒዓለም ቤ/ክ በሊቢያ ለተገደሉ ወገኖቻችን ጸሎት ላይ የተገኙ ምዕመናን
ከሥርዓተ ጸሎቱ ፍጻሜ በኋላ አቶ ታምራት አዳሙ የሰበካ ጉባዔው ሰብሳቢ የሞቱት ወገኖቻችንን በማስመልከት ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ ካራ መዝዘው ግድያ የፈፀሙ ኃይሎች የማንንም እምነት ተከታይ እንደማይወክሉ ገልጠዋል። “ለዚህም ምሳሌ ሊሆን የሚችለው የሙስሊም እምነት ተከታዮች ሳይቀሩ በአሁን ሰዓት በዚህች ቤተክርስቲያን መገኘታቸው ነው” ብለዋል።
ከዚህ በመቀጠል ወገኖቻችንን በማሰብ በደብሩ መዘምራን ኀዘናዊ መዝሙር ቀርቦ፣ ከመካነ ኢየሱስ የመጡት ቄስ ዮናስ ቤተክርስቲያኒቱን በመወከል ለምዕመናኑ ትምህርት ሰጥተዋል። በትምህርታቸውም “የሌላው መከራ ለእናንተም እንዲሆን አድርጉ” የሚል የመጽሐፍ ቃል በመጥቀስ አስተምረዋል።
በስቶክሆልም መድኃኒዓለም ቤ/ክ በሊቢያ ለተገደሉ ወገኖቻችን ጸሎት ላይ የተገኙ ምዕመናን
አቶ ሶፊያን የእስልምና ዕምነትን በመወከል ትምህርታዊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ከተገደሉት ውስጥ አንዱ ሙስሊም መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ የእስልምና ተከታይ ወገኖቹ ላይ ካራ እንዲመዝ ተጠይቆ እምቢ በማለቱ ከክርስቲያን ወገኖቹ ጋር አንድ ላይ እንደተገደለ ገልጠዋል። በማጠቃለያቸውም ለዚህ ሁሉ አስከፊ መከራና ስደት የተዳረግነው አንድነት ስለጎደለን መሆኑን በመጥቀስ፤ ከዚህ በኋላ በኃይማኖት፣ በዘር፣ … ሳንከፋፈል አንድነታችንን አጠናክረን መጓዝ ይገባናል ብለዋል። ኢትዮጵያዊው የወገኖቹን ኀዘን ለመወጣት በጋራ በመሰባሰቡ ምስጋና አቅርበዋል። ይህ ጭካኔ በእስልምና ስም የተሰራ ደባ እንጂ የእስልምና ኃይማኖትን እንደማይወክል ገልጠዋል።
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ አስቀድመው የተናገሩትን የእስልምና እና የመካነ ኢየሱስ ኃይማኖት ተወካዮችን መርቀው፣ የተናገሩት ከእውነት ያልራቀ መሆኑን ገልጠዋል። “የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስል ጊዜ ይመጣል” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል በመጥቀስ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል። የተሻለ ሠይጣን ተባርሮ፣ የከፋ ሠይጣን ሊቢያ ውስጥ እንደመጣ ጠቅሰው፤ የወገኖቻችን ሞት፣ ሞት ሳይሆን ሰማዕትነት እንደሆነ አስተምረዋል። ይህም የሁለተኛው ዘመን ቃል እንደተፈጸመ ይቆጠራል ብለዋል። ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ሰማዕታት ይህን በመሰለ አሟሟት እንደሞቱ አስታውሰዋል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በምስጢር እንደሚጠብቃት ገልጠው፣ “አሁንም እግዚአብሔር በምስጢር ይጠብቀን! ለችግራችንም እግዚአብሔር አምላክ መፍትሄ ይስጠን! የወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን! በቅርቡም ከሲኖዶስ ትልቅ ውሳኔ ይተላለፋል” በማለት ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል።
በስቶክሆልም በደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን
150422-stockholm-medhanialem-01

No comments:

Post a Comment