Wednesday, November 4, 2015

አወዛጋቢው ሮበርት ሙጋቤ ኬንያውያንን “ስርቆት በደማችሁ ነው ያለው!” በማለት ወረፏቸው!



ባለፈው እሁድ አንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ለተገኘው ህዝብ ባደረጉት ንግግር ሙጋቤ ኬንያውያን ላይ ከፍተኛ ውርጅብኝ አውርደዋል.
“እነዚህ የምስራቅ አፍሪካ ሰዎች በህዝባቸው ላይ የሚያደርጉት ዘረፋ እጅግ ያስደነግጣል. እንድያውም አንዳንዴ ስርቆት በደማቸው ውስጥ ያለ ይመስለኛል. ኬንያውያን ወደ ተለያዩ ኮሌጆች ይሄዳሉ, ምርጥ የተባለ ትምህርት ይማራሉ, በስተመጨረሻም ምርጥ ሌቦች ሆነው ይመረቃሉ.” በማለት የራሳቸውን ህዝብ ከዚህ አይነት ተግባር ተጠበቁ በማለት ማስተማርያ አድረገዋቸዋል. “ሀገሩን የሚያፈቅር ዜጋ ፈጽሞ ከሀገሩ አይሰርቅም!” በማለት መክረዋል.
ይህንንም ተከትሎ በቁጣ የተሞሉ ኬንያውያን በትዊተር ገጾቻቸው ላይ ለሙጋቤ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው.
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ከኬንያ ሌላ ጉድ ተሰምቷል. አንድ የኬንያ የሚኒስቴር መስርያ ቤት በአመቱ ከገዛቸው የንብረት ዝርዝሮች ውስጥ ኮንደምን ማስገባቱ እጅግ አስገራሚ ሆኖ እየተዘገበ ነው. ይሄው መስርያ ቤት ምንም እንኳ ለምን አገልግሎት እንደሸመተው ይፋ ባይደረግም አንድ ፓኬት ኮንዶም በ 450 የሀገሪቱ ገንዘብ መግዛቱን በበጀት ዝርዝር ውስጥ ማስገባቱ ተነግሯል.
ይህም ብቻ ሳይሆን ለመቶ የኮምፕዩተር ኪቦርዶች 4 ሚሊየን, ለ 20 ፍሬ እስክሪፕቶዎች 174,000 እና መሰል የተጋነኑ የክፍያ ዝርዝሮቹ ይፋ ሆነዋል.
ድሮ ድሮ አፍሪካ የኋላ ቀርነቷ ምክንያት መሀይምነት ወይም ጦርነት ነው ይባል ነበር. አሁን ግን ስልጣን በጨበጡ በሀገሯ ልጆች እየተበዘበዘች ሀብቷ በሙሉ እየተሟጠጠ በጥቂት ቤተሰቦች እና የአንድ ወገን ሰዎች እጅ ስር በመውደቁ ምክንያት ነው. አፍሪካ ዛሬም የእርዳታና የብድር እጆቿን ከመዘርጋት አልተቆጠበችም.ይሁን እንጂ በዚህ መልክ የምታገኛቸውን ገንዘብ በሙሉ ትዘረፋለች.
የሆነ ሆኖ ዛሬ ኬንያ እንዲህ በሙስና ይሄ ሁሉ ውርጅብኝ የሚደርስባት ከሌሎች የምስራቅም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ መልኩ የሚፈጸም ሌብነት ስላለባት አይደለም. ልዩነቱ ኬንያ አይንና ጆሮ የሆኑ, ቀንና ማታ ተግተው መረጃ ለህዝብ የሚያቀብሉ ለቁጥር የሚታክቱ የመገናኛ ብዙሀን ስላሏት ነው.
በኬንያ በየቀኑ የሚታተሙት ጋዜጦች, ሳምንታዊ መጽሄቶች, የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጣብያዎች ከምንም ነገር ቅድምያ የሚሰጡት ወሬ ቢኖር ሙስና ነው. በኬንያ ስለ ሙስና ሳይዘገብ ጸሀይ ወጥታ አትጠልቅም.የሚገርመው ነገር ደግሞ አንዳንድ ጊዜ አስር ብር ስለተቀበለ አንድ ተራ ባለስልጣንና የፍርድ ቤት ሂደቱ ሁሉ ሳይቀር ይዘገባል. ይህ ነው ኬንያን ፊት ለፊት ያደረጋት. እንጂማ ሌብነቱ በብዙ መልኩ በየሀገሩ የምናየው ነው.
የሚዲያን ባህሪ ቀድመው የተረዱና ራሳቸውን በስልጣን ከልለው የህዝብ ደም የሚመጠምጡ በርካታ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፎቅን የሚያህል የሀገር ንብረት ሲሰርቁ እንኳ አይነቃባቸውም. ምክንያቱም አስቀድመው የመገናኛ ብዙሀኑን አፍ ዘግተዋልና. “ሞኝ ዝም ቢል ጠቢብ መሰለ” ይላል መጽሀፉ. እነዚህም ስለሰሩት ሀጢያት የሚናገር ቢጠፋ ጻድቃንና ጨዋ ሆነው ታዩ.

No comments:

Post a Comment