
ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መሆን እና አለመሆኑ የሚታወቀው ከውጤቱ ወይም በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ሳይሆን ከድምጽ አሰጣጡ በፊት በነበረው ሒደት ጭምር መሆኑ ይነገራል። አገራችን ኢትዮጵያም የፊታችን ግንቦት 16 ቀን አምስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባገኘነው መረጃ መሰረት 58 ፓርቲዎች በምርጫው ለመሳተፍ 1018 እጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል። ዘጠኝ የግል ተወዳዳሪዎችም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር በእጩዎች ምዝገባ ላይ ስማቸውን አስፍረዋል። ካለፉት አራት ምርጫዎች በቂ ትምህርት በመውሰድ መጠነ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ የአሁኑን ምርጫ ካለፉት በተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ዝግጅት እንዳደረገ የሚገልጸው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ግን አመኔታ ያገኘ አይመስልም። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች “የቦርዱን ቃል ለማመን ይከብደናል፤ እንዲያውም ካለፉት ሁሉ በባሰ የፖለቲካ ምህዳሩ የጠበበበት ወቅት ነው” ሲሉ ይከሳሉ። ዝግጅት ክፍላችንም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተያየት በመያዝ ከዚህ በታች እንዲህ ያቀርበዋል።
ቅድመ ምርጫው ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ
ዊኪ ፔዳ የተባለው ድረ ገጽ የመራጮች ምዝገባ የምርጫው የመጀመሪያ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በ2015 ባወጣው እትሙ ይገልጸዋል። ድረ ገጹ የመራጮች ምዝገባ ለምርጫ ወሳኝነቱን በገለጸበት ዘገባው “መራጮች በህግ ከተከለከሉና የመምረጥ መብት ከሌላቸው ሰዎች ውጭ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በምርጫው በንቃት መሳተፍ አለባቸው” ይላል። በዚህ በኩል ከ90 ሚሊዮን የማያንስ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ በምርጫው በመራጭነት መሳተፍ ያለባቸው ዜጎች ምን ያህሉ ናቸው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ምን ያህሉ ዜጎች በፍላጎታቸውና ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለመራጭነት ተመዝግበው ካርድ ወስደዋል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመሄድ ለማጣራት ሞክረናል። ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው 38 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች ለመራጭነት መመዝገባቸውን ያመለክታል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትናንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ ላይ እንዳስታወቀው ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ ቅድመ ምርጫው በስኬት መጠናቀቁን በቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና አማካኝነት አስታውቋል። የመራጮች ምዝገባ እንከን አልባ ነው የተባለው ስህተት መሆኑን የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለለዓላዊነት(ዓረና) ወክለውበመቀሌ ከተማ የሚወዳደሩት ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ “በመራጮች ምዝገባው ወቅት የሚፈልጉትን ከቤቱ ድረስ እየሄዱ ካርድ ሲሰጡ የማይፈልጉትን ሰው ግን ለመመዝገብ ሲሄድ ካርድ ጨርሰናል እያሉ ይመልሳሉ። ለዚህ አንዱ ምሳሌ እኔ ነኝ። እኔ በመቐለ ከተማ ተወዳዳሪ ብሆንም የመራጭነት ካርድ የለኝም” ሲሉ ይናገራሉ። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን ለመራጮች ምዝገባ በተፈቀደው ቀን ሂዶ የተመዘገበ በሙሉ ካርድ ተቀብሏል ሲል ይናገራል።
የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አዳነ ታደሰ “የምርጫ ቦርድ መረጃ ምን ያህል ትክክል ነው ብሎ ማመን ባይቻልም ሪፖርቱ ትክክል ከሆነ የመራጩ ህዝብ ተሳትፎ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል” ሲሉ ይናገራሉ።
የዕጩዎች ምዝገባ
ከገዥው ፓርቲ ውጭ ሌሎች ፓርቲዎች በሙሉ በምርጫ ቦርድ ላይ ተመሳሳይ ቅሬታ ከሚያቀርቡባቸው ነጥቦች አንዱ የእጩዎች ምዝገባ ነው። የኢዴፓ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አዳነ ታደሰ ፓርቲያቸው 280 እጩዎችን ቢያስመዘግብም ምርጫ ቦርድ ግን በመጨረሻ የእጩዎች መዝገብ ላይ ስማቸውን ያስተላለፈው የ177 እጩዎቻቸውን ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።
ከአቶ አዳነ ሃሳብ ጋር የሚስማሙት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ናቸው። አቶ ዮናታን በተለይ ለሰንደቅ እንደገለጹት ሰማያዊ ፓርቲ ከ400 በላይ እጩዎችን ቢያስመዘግብም 179 እጩዎቹ ብቻ ለመጨረሻው የቅጽ አራት መዝገብ ላይ እንደሰፈሩ ተናግረዋል።
አቶ ዮናታን ተስፋዬ አያይዘውም “ፓርቲያችን ካቀረባቸው እጩዎች መካከል ከ200 በላይ የሚሆኑትን ቦርዱ ሰርዞብናል። አንዳንዶቹን በፍርድ ቤት ለማየት ሞክረናል። ፍርድ ቤቱ ግን ፍትህ ሊሰጥ አልቻለም” ያሉ ሲሆን የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ አዳነ ግን “የእጩዎች ምዝገባ ያለምንም እንከን የተጠናቀቀ ነው ማለት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።ሙሉውን ለማንበብ ይህን ይጫኑ
በይርጋ አበበ
ምንጭ ሰንደቅ
No comments:
Post a Comment