ባለፉት 11 ወራት ከዜጐች ለኮሚሽኑ የቀረቡ አቤቱታዎች በቁጥርም በዓይነትም ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነፃፀሩ መብዛታቸውን ሰምተናል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት ከቀረቡት 1 ሺህ 419 አቤቱታዎች መካከል 999 ያህሉ ተቀባይነት ያላገኙባቸው ምክንያቶች መካከል፣ አቤቱታዎቹ ከወንጀል ወይም ከሙስና ጋር የተገናኙ መሆናቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡
በተጨማሪም ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ የደረሱ ተደራራቢ በደሎች ሆነው ከዚህ ቀደም ለእንባ ጠባቂ የቀረቡ ሆነው ስለተገኙ አቤቱታዎቹ በኮሚሽኑ ተቀባይነት አላገኙም ብለዋል፡፡
አንዳንዶቹ አቤቱታዎች ደግሞ የቀረቡት ከአዕምሮ መታወክ እና ከስነ-ልቦና ችግር የመነጩ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ በመሆኑም 999ኙ አቤቱታ አቅራቢዎች የተሸኙት የምክር አገልግሎት ብቻ ተሰጥቷቸው እንደሆነ ከኮሚሽነሩ ሰምተናል፡፡
ወሬውን የሰማነው ዛሬ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑን የ11 ወር እቅድ አፈፃፀም ሲመረምር ነው፡፡
የመብት ጥሰት ደርሶብኛል ብለው በግልና በቡድን ለኮሚሽኑ አቤት ካሉት 1 ሺህ 419 አቤቱታ አቅራቢዎች መካከል ተቀባይነት ያገኙት 330 ብቻ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡
የመብት ጥሰት ደርሶብኛል ብለው በግልና በቡድን ለኮሚሽኑ አቤት ካሉት 1 ሺህ 419 አቤቱታ አቅራቢዎች መካከል ተቀባይነት ያገኙት 330 ብቻ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡
የቀረቡትን ቅሬታዎች በመመርመርና በማስማማት መፍትሄ የተሰጣቸው ለ264 አቤቱታዎች ነው፡፡
ሌሎች 47 አቤቱታዎች በመረጃ እጦትና በተለያየ ምክንያት እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡
ቀሪዎቹ 78 አቤቱታዎች ደግሞ ጉዳዩ ያገባቸዋል ወደተባሉ መሥሪያ ቤቶች በደብዳቤ መሸኘታቸውን ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ተናግረዋል፡፡
አሁንም በምርመራ ላይ ያሉ 19 አቤቱታዎች መኖራቸውን የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ባለፉት 11 ወራት ከዜጐች የሚቀርቡ አቤቱታዎች በቁጥርም ሆነ በዓይነትም ጨምረዋል፡፡ አብዛኞቹም የመልካም አስተዳደር እጦት ናቸው ብለዋል፡፡

No comments:
Post a Comment