ከባድ መሳሪያ የተያዩ ወታደራዊ ሎጀስቲክንና የዓየር መቃወሚያዎችን ጨምሮ ለጊዜው ምንነታቸው በግልፅ ሊለዩና ሊታወቁ ያልቻሉ ቁሶችን የጫነ ኮምቮይ ከመሀል አገር ተነስቶ ወደ ፆረና እያመራ ነው። ዳግም ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው በሁለቱ ሀገራት ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው በመሄድ ላይ መሆናቸውን መረጃውን ካከባቢው ያደረሱን ያይን እማኞች በመናገር ላይ ይገኛሉ ። የብዙሀኑን ፖለቲከኞችና ወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ትናንሽ ትንኮሳዎችና ግጭቶች ወደ ለየለት ጦርነትና እልቂት መሸጋገራቸው አይቀርም የሚለውን ግምትና ጥርጣሬ ትክክለኛነት በሚያረጋግጥ መልኩ በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ለህዝባቸው ይፋዊና ግልፅ ባልሆነ መልኩ በከፍተኛ ወታደራዊ ሚስጥርነት ተይዞ በመከናወን ላይ የሚገኘው የጦርነት ዝግጁነት የሚፈለገውን የማጥቃትና የመከላከል አቅሙ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስም ሁለቱም መንግስታት ዝምታን መርጠዋል ። ይህን ተከትሎ በዚህ ውጥረትና አለመረጋጋት በሰፈነበት የድንበር አዋሳኝ ክልሎች እና ቀበሌዎች ከጠላት ወገን ሊደርስ የሚችለውን ወረራና የማጥቃት እርምጃ ለመከላከልና ሲመችም ድንገተኛ አደጋዎችን ለመጣል ሲባል በአካባቢው የሚደረገው ያልተለመደ እንቅስቃሴና ወታደራዊ ሰፈራ ያሳሰባቸው ሰላማዊ ዜጎችም ለሀጥያን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል በማለት የመኖሪያ ስፍራቸው ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጦርነት አውድማ ከመቀየሩ በፊት ከብቶቻቸውንና ንብረቶቻቸውን በመያዝ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በገፍ በመሰደድ ላይ ይገኛሉ። በተያያዘ መረጃ የኢህአዴግ መንግስት በስሩ በሚገኙ ሚዲያዎቹ በኩል በተደጋጋሚ ይፋ እንደሚያደርገው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አርበኞች ግንቦት ሰባት እያገኘ የመጣው ህዝባዊ ድጋፍና የተደራጀ ጦር በይፋ ያሳስበኛል ለማራምደው ስርዓትም የሽብርና የስጋት ምንጭ ሆነዋል በማለት መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ነው
