Monday, July 25, 2016

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኮርፖሬሽን ካሉት 41 ባቡሮች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡት ከ28 አይበልጡም መባሉ

ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኮርፖሬሽን ካሉት 41 ባቡሮች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡት ከ28 አይበልጡም መባሉን ስሰማ — ድንግጥ ነው ያልኩት፡፡ (ኮርፖሬሽኑ የእኔን ያህል እንኳን የደነገጠ አይመስለኝም?!) ባቡሮቹ በችኮላ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉና ከቻይናው ድርጅት ጋር በተገባው ውል ላይ የባቡር መለዋወጪያ እንዲያቀርብ የሚያስር ስምምነት ሳይደረግ መቅረቱ ለተፈጠረው ችግር ሰበብ ሆኗል፤ ተብሏል፡፡ … ይሄም የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ከተባለ ያመኛል፡፡ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ይቀርፋሉ ተብለው በከፍተኛ ወጪ፣ ያውም በብድር የተገዙት እነዚህ ባቡሮች፤ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጥገና ማሳለፋቸው አሳሳቢ ነው፤ የተባለ ሲሆን፤ ባቡሮቹ መንገዱ ምቾት እየነሳቸው አልፎ አልፎ ከተዘረጋላቸው ሃዲድ እንደሚወጡ፣ በዚህም ሳቢያ ሃዲዱ እንዲጠረብና በግራሶ እንዲለሰልስ መደረጉ ታውቋል፡፡ ይታያችሁ … ከዓመት በኋላ 40 የነበረው በእጥፍ ጨምሮ 80 ባቡሮች ሲርመሰመሱ እናያለን ብለን ተስፋ ያደረግነውን ሁሉ ኩም አደረጉን!… 13 ባቡሮች ከቆሙ ምን ቀረን?! በቴክኒክ ብልሽትም ቢሆን ለምን ይቆማሉ አልወጣኝም፡፡ ተጠግነው በጊዜ ለምን ወደ ሥራ አይገቡም ነው ጥያቄው፡፡ ችግሩን የሚፈታ የባቡር መለዋወጪያ አቅራቢ የለም ተብሏል፡፡ (“ዊርድ” አለ ፈረንጅ!)
እኔ የምለው ግን … ሃዲዱን የሰራው የቻይና ኩባንያ ነው!! ባቡሩን ያመረተው የቻይና ፋብሪካ ነው!! የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለ3 ዓመት የሚመራው የቻይና ማኔጄመንት ነው!! የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኮርፖሬሽን ውል እንኳን መፈራረም ያቅተው? የፈሰሰ ውሃ አይታፈስምና አሁን የሚያዋጣው ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ መዘየድ ብቻ ነው፡፡ የተሰራው ጥፋት (ስህተት) እንደተለመደው በዝምታ ይታለፍ ግን አልወጣኝም፡፡ “የህዝብ ሀብት ኪሳራ በስኳር ኮርፖሬሽን ይብቃ!”

No comments:

Post a Comment