የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከትናንት በስተያ ምሽት ላይ ባወጣው ማስጠንቀቂያ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ አማራና ኦሮምያ ክልሎች ውስጥ በቀጠለው ለብዙ ሕይወት መጥፋት፣ በሺሆች ለሚቆጠሩ ሰዎች መታሠርና መጎዳት እንዲሁም ለተከታታይ የንብረት ውድመትን ምክንያት በሆነው አለመረጋጋት ምክንያት አሜሪካዊያን ወደ ኢትዮጵያ ለማድረግ የያዙትን እጅግ አስፈላጊ ያልሆነ የጉዞ ውጥን ሁሉ እንዲሠርዙ አሳስቧል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ ውስጥ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት የአሜሪካ ኤምባሲ በብዙ የሃገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የቆንስላ አገልግሎት ለመስጠት ያለው ችሎታ የተወሰነ መሆኑንም ይኸው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከመስከረም 28/2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን መግለጫው አስታውሶ ጥቅምት 5/2009 ዓ.ም በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እርምጃዎች አፈፃፀም መመሪያ መሠረት ግለሰቦች ወትሮ የተፈቀዱ የነበሩ ግንኙነት ማድረግን፣ መገናኛ ብዙኃንን መከታተልን፣ በስብሰባዎች ላይ መሣተፍን፣ ከሌሎች መንግሥታት ወይም ከውጭ ድርጅቶች ጋር ግንኙነቶችን ማድረግን፣ የሰዓት እላፊ ገደብን መጣስን የመሳሰሉ ተግባራት ውስጥ ቢገኙ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊታሠሩ እንደሚችሉ አሳስቧል፡፡
መመሪያው የዩናይትድ ስቴትስና የሌሎችም ሃገሮች ዲፕሎማቶች ለመንግሥት ቀድመው ሳያሳውቁና ፍቃድ ሳያገኙ ከአዲስ አበባ ከአርባ ኪሎ ሜትር ርቀት ዘልቀው እንዳይጓዙ የሚከለክል መሆኑ የአሜሪካ ኤምባሲ ለዜጎቹ ድጋፍ ለመስጠት ያለውን አቅም በብርቱ እንደሚጎዳው መግለጫው አስረድቷል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ መመሪያው ሙሉ ቃል በአሜሪካ ኤምባሲ ዌብ ሳይት ላይ ሠፍሮ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
የኢንተርኔት፣ የሞባይል ዳታና የስልክ አገልግሎቶች በመላ ሃገሪቱ ውስጥ በየወቅቱ ወይም ሙሉ በሙሉ የሚቋረጡ መሆናቸውም ኤምባሲው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት የሚያስተጓጉል መሆኑንም የጉዞ ማስጠንቀቂያው አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ ዜጎቹ አማራጭ የግንኙነት ዝግጅቶች እንዲኖሯቸውና ያለውን ሁኔታም ለቤተሰብና ለወዳጆቻቸው እንዲያሳውቁም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መክሯል፡፡
የፀጥታ ማሳሰሲያ መልዕክቶችን ከአሜሪካ ኤምባሲ ለማግኘት መመዝገብ የሚቻልበትን ሁኔታ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው በዚህ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሠነድ መጨረሻ ላይ አስፍሯል፡፡ (ከሥር ከተቀመጠው የእንግሊዝኛው የማስጠንቀቂያ ሠነድ በታች ማግኘት ይቻላል፡፡)
ዜጎቹ ሠላማዊ ሰልፎችና ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ፣ አካባቢዎቻቸውን ያለመታከት እንዲያጠኑና የሚገኙበትን የግል ደኅንነት ሁኔታ እንደዲገመግሙም የማስጠንቀቂያ ሠነዱ መክሯል፡፡
መንግሥቱ ለሰልፎች ምላሽ ለመስጠት ኃይል ሊጠቀምና ቀጥታ ተኩስ ሊከፍትም እንደሚችልና ሰላማዊ ይሆናሉ የተባሉ ሰልፎችም ያለማስጠንቀቂያ የኃይል ብተና እርምጃ ሊወሰድባቸው ወይም ሰልፎቹ ወደ ሁከት ሊለወጡ እንደሚችሉ ዜጎቹ እንዲያስታውሱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አስጠንቅቋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች የደኅንነት ሁኔታቸውን እንዲከታተሉና በፍጥነት መውጣት ካለባቸውም ሊጠቀሙበት የሚችሉት አማራጭ ዕቅድ እንዲያዘጋጁም አሳስቧል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሠራተኞች ኦሮምያን፣ አማራን፣ ሶማሊን፣ ጋምቤላን፣ ደቡብ ኢትዮጵያን ክልሎችና የኢትዮጵያና የኬንያ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያና የኤርትራን የድንበር አካባቢዎች ጨምሮ ወደ ብዙ የሃገሪቱ ክፍሎች የግል ጉዞዎችን እንዳያደርጉ የተገደቡ መሆናቸውንም መግለጫው አመልክቶ ለሥራ የሚደረጉ ጉዞዎች በተናጠል እየታዩ እንደሚፈቀዱም ገልጿል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሠራተኞች ወደ አዲስ አበባና አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ገደብ መጓዝና መንቀሳቀስ እንደሚችሉ የማስጠንቀቂያው ሠነድ ጠቁሟል፡፡
በአካባቢው ስላለው የአል-ሻባብ እንቅስቃሴ፣ የውንብድና ቡድኖች እና ሌሎችም የደኅንነት ሥጋቶች ኢትዮጵያን በሚመለከተው የመረጃ ምዕራፍ የደኅንነት ክፍሉን ሠነዶች እንዲያዩ መግለጫው መክሯል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግንኙነት ሁኔታ ለመተንበይ አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች በስማርት ትራቭለር ኢንሮልመንት ፕሮግራም – ኤስ.ቲ.ኢ.ፒ. /ስቴፕ/ ከሚያደርጉት ምዝገባ በተጨማሪ በቴክስት ወይም ኤስኤምኤስ የደኅንነት መረጃ ማግኘት እንዲችሉ የሞባይል ስልክ ቁጥሮቻቸውን ለኤምባሲው እንዲያስመዘግቡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
No comments:
Post a Comment