Sunday, April 23, 2017

ኦፌኮ’ ህልውናው ሊያከትም ነው ፤ የምርጫ ቦርዱ ፕሮፌሰር በቃና ታሪካዊ ውሳኔ ይጠበቃል


በኦሮሚያ ሰፊ ድጋፍ ያለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ኦፌኮ ህልውናውን ጠብቆ የመቆየት እድል እንደሌለው ለምርጫ ቦርድና ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው የኦህዴድ ሰዎች ለዛጎል ገለጹ። እንደ ገለጻው ኦፌኮ እንደ ፓርቲ እንዲቆይ የማይፈለገው በሁለት አበይት ምክንያቶች ነው።
የመጀመሪያው ከኦነግ በሁዋላ ኢህአዴግን የፈተነው ኦፌኮ በመሆኑና ሰፊ ድጋፍ ስላለው በዚህ መልኩ ሕዝብ የሚደግፈው ድርጅት በተለይ ኦሮሚያ ላይ እንዲኖር ስለማይፈለግ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ቀጣዩን ምርጫ ኦሮሚያ ላይ ማሸነፍ ስለማይቻል ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ በሚል እንደሆነ የመረጃው ባለቤቶች ያስረዳሉ። በሌላም በኩል ከድርድር የወጣው መድረክም ኦፌኮን ካጣ ባዶ እንደሚሆን በማሰብም ጭምር ነው ሲሉ ያክላሉ።
ኢህአዴግ ያቋቋመውንና በቀደሞው የምርጫ ቦርድ ሹም የሚመራው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርት ያስታውሱት ክፍሎች፤ በሪፖርቱ ከተወነጀሉት ሶስት ፓርቲዎች መካከል ኦፌኮ አንዱ መሆኑን ይታወሳል። ሰማያዊ ፓርቲና የጌዲዮ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እና ኦፌኮ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ “እንዲቀሰቀስና እንዲባባስ አድርገዋል” በሚል የቀረበውን ሪፖርት ሸንጎው አጽድቆ ፓርቲዎች እንዲከሰሱ ወሳኔ አስተላልፎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ለገለልተኛ አጣሪዎችና ለተባበሩት መንግስታት መርማሪዎች በሩን የዘጋው ኢህአዴግ፣ ሕዝባዊ አመጹን ተከትሎ ለጠፋው የሰው ህይውት ነጻና ገለልተኛ አጣሪዎች ምርመራ እንዳያደርጉ ሲከለክል ምክንያት አቅርቦ ነበር። ምክንያቱም ” ሉአላዊነትን የማስደፈር ያህል ነው” የሚል ነበር። ኢህአዴግ ይህንን ቢልም በአገሪቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ተጥሶባቸዋል የሚባሉ አካባቢዎችን ለጋዜጠኞች፣ ለለጋሽ አካላትና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለምልከታ ሲከለክል ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የሚገልጹ አሉ።
የዜናው ሰዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ የሚፈራው ከውጪ ያሉ ተቃዋሚዎችን አይደለም። የአንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ስም በመጥራት እነዚሁ ክፍሎች እንደተናገሩት ኢህአዴግ አገር ቤት ተነስቶ የነበረው ተቃውሞ አይነት ቀውስ በድጋሚ እንዳይፈጠር “የተኛውንም ርቀት” ይሄዳል። ከተፈጠረም በየትኛውም ወቅትና ሰዓት የወታደራዊ መንግስት ለማወጅና አገሪቱን “በይፋ” በወታደራዊ ስር ለማሰተዳደር ዝግጁ ነው።
በዚሁ መነሻ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ተቀባይነት ያላቸውን የኦፌኮን መሪዎችና ራሱን ፓርቲውን አግዶ ህልውናውን ማክሰም ሆን ተብሎ ሲሰራበት የነበረ ጉዳይ ነው። ይህንኑ እቅድ ተግባራዊ ለማደረግ ደግሞ ” ህግ” የሚባለውን ማደናገሪያ መጠቀም ግድ በመሆኑ ገለልተኛ እንዳልሆነ በየተኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚታወቀውን የ” ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ” ሪፖርት መጠበቅ ግድ ነበር። ዜናውን የጠቆሙት የኦህዴድ ሰዎች ” ክስ እንዲመሰረት የተወሰነባቸው ፓርቲዎች ሲከሰሱ በጥቅሉ ምን እንደሚወሰንባቸው ባይታወቅም ኦፌኮ ግን እንደሚታገድና፣ የምርጫ ቦርድ የእውቅና ማስረጃን እንደሚነጠቅ፤ በዛውም እንደሚከስም፣ ሌላ ሕዝብ የሚያምናቸው ድርጅቶች እስኪበቅሉ ምርጫውም ያልፋል ” ብለዋል።
ዶክተር መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገርባ ፣ ያለተዘመረለት ኦልባና ሌሊሳ እና በርካታ አመራሮቹን፣ አባላቱን፣ ደጋፊዎቹ እስር ላይ ያሉት ኦፌኮ መጪው ዕድሉ እንደተባለው መክሰም ከሆነ ይህንን ወሳኔ የሚወስኑት ፕሮፌሰር በቃና – የምርጫ ቦርድ “ዋና ሃላፊ” መሆናቸው ታሪኩን፣ አጋጣሚውን፣ እንዲሁም ውሳኔውን ልዩ እንደሚያደርገው ከኦህዴድ ሰዎች የተገኘው ዜና ያስረዳል።
የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑንን ሪፖርት በተለያየ መልኩ ከመዘገብ ውጪ በኦፊሳል የተጠቀሱት ፓርቲዎች ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድ የተባለ ነገር የለም። ይሁንና ተጠያቂ እንዲደረጉ መወሰኑ የዜናውን ተአማኒነት ያጎላዋል የሚል እምነት አለ። ኦፌዴን ሰማያዊ ፓርቲና የጌዲዮ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የተወሰነባቸውን ውሳኔ አስመልክቶ የሰጡት ” በገለልተኛ ወገን ያልቀረበ ሪፖርት ተቀባይነት የለውም” ሲሉ መመለሳቸው አይዘነጋም።

የዶ/ር መረራ ፓርቲ ቀደም ሲል ስሙ ተነጥቆ ለአቶ ቶለሳ ቢሰጥም በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርክሩን አቁመው ኦፌኮን ማቋቋማቸው አይዘነጋም። ኢህአዴግ የሚወዳደረው ፓርቲ ሲፈጠር ስሙን መንጠቅና ለሌላ አሳልፎ የምስጠት፣ አመራሮቹን አስሮ የማዳከም ለዩ ባህሪው እንደሆነ በስፋት የሚከሰስበት ጉዳይ ነው። አሁን በድርድር ላይ ያሉትን ፓርቲዎች ታሪክ ማየትም ይህንኑ ሃቅ ያጎላዋል።88c6732c

No comments:

Post a Comment