Wednesday, May 4, 2016

በኢትዮጵያ በሕግ ሽፋን የዜጎችን መብት መጣስ ተባብሶ መቀጠሉን ሂውማን ራይት ሊግ አስታወቀ


ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያ ውስጥ የፀረ ሽብር ሕግን ከለላ በማድረግ መብታቸውን የሚጠይቁ ዜጎችን ማሰር፣ መግደልና ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸም ተጠናክሮ መቀጠሉን የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ ገልጿል። ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል የበርካታ ንጹሃንን ሕይወት የቀጠፈው ዘግናኝ እልቂት በህወሃት ኢህአዴግ መራሹ ገዥ ቡድን የተቀነባበረ መሆኑን አስታውቋል።
ይህን ኢሰብዓዊ እልቂት ተቃውመው ለመብታቸው የታገሉት ከ 22 በላይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የሃሰት ክስ እንደተመሰረተባቸው አመልክቶ ፣ በህወሃት የተቀነባበረ ሴራ በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ካለ ፍትሕ በእስር ቤት እየማቀቁ ነው ብሎአል።
በኢትዮጵያ ያለው የፀረ ሽብር ሕግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በሚጻረር መልኩ የወጣ ሲሆን ይህም የዜጎችን የመጻፍ፣ የመናገርና የመቃወም ሕገ መንግስታዊ መብቶችን በሚጥስ መልኩ ሆን ተብሎ ተረቆ በሥራ ላይ መዋሉን አስታውቋል።
በኦሮሚያ የተነሳውን ሰላማዊ የዜጎችን ጥያቄ በመደገፍ ከሕዝባቸው ጋር በመሆን ሲቃወሙ ከነበሩት ውስጥ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የፓርቲው ፀሃፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ አቡላና ሌሎችም በፈጠራ የሽብር ክስ መከሰሳቸውንና የመብት ጥሰቱ ተባብሶ መቀጠሉን ሪፖርቱ አመላክቷል።
መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በሽብር ሕግ ስም አላግባብ ታስረው የሚገኙ ንጹሃን ኢትዮዮጵያዊያንን ህወሃት መራሹ መንግስት ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታዎች ክሳቸውን በማንሳት ሊፈታቸው ይገባል ብሎአል።

Tuesday, May 3, 2016

ሰበር ዜና —4 የህወሃት ብሄራዊ መረጃ ከፍተኛ ሚስጥራዊ አባላት ተገደሉ


የብሔራዊ መረጃ የቅድመ ዝግጅት ማሰራጫና ማከናወኛን ክፍል መሰረት ባደረገ መልኩ ለመረጃ ክፍሉ ሐገር ለሐገር እየተዟዟሩ ሲሰልሉና ወሬ ሲያቀብሉ እንዲሁም ያለአግባብ ወገኖቻችንን ሲያሳስሩና ሲያስገድሉ የነበሩ አራት ቁልፍ የህወሃት ደህንነት አባላቶች መገደላቸዉን ታማኝ የመረጃ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል። ተጠሪነታቸዉ ለመረጃዉ ክፍል ዳይሬክተር ብቻ እና በከፍተኛ ሚስጥር ከሌሎች አባላት እንኳ በተሰወረ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ብዛት ያላቸዉ አባላቶች ላይ እርምጃዎቹ ያነጣጠሩ ናቸዉ ሲሉም ምንጮቻችን የገለጹ ሲሆን እርምጃ የተወሰደባቸዉ ግለሰቦችን ስም ዝርዝር ከዚህ በታች አስቀምጠዋል ።
1. አቶ በኩር ባዘዘዉ ገብረህይወት
2. ቀሲስ ትንሳኤ ሃይለ መለኮት
3. ሲስተር ሳምራዊት በቃሉ
4. መምህር ጣፋ አጋፋሪ
በየካቲት 28/2008 ለመረጃዉ ክፍል የወረደዉ የሞት መርዶ ብዙዎችን ያስደነገጠ ከመሆኑን ባሻገር የአራቱም ግለሰቦች አሟሟት በተመሳሳይ ወቅትና በተለያየ ክልል መሆኑ እንዲሁም አራቱም ከተገደሉ በኋላ ለመረጃ ክፍሉ ካልታወቁ ግለሰቦች የስልክ ጥሪ ተደርጎ በሐገሪቷ ላይ እየተካሄደ ያለዉ አፈናና ግድያ እስካልቆመ ድረስ እርምጃዉ እንደሚቀጥል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ዉጥረቱን አባብሶታል።
በተለይም በኦሮሚያ ክልል እና በጎንደር እንዲሁም በኦጋዴን ክልል አካባቢ ተሰማርተዉ የነበሩ የመረጃዉ ክፍል ሰራተኞች በሙሉ እርምጃ ሊወሰድባቸዉ እንደሚችል የጠቆሙት ምንጮቻችን በእነዚህ ክልል የተሰማሩ አባላቶች ጠርገዉ እየወጡ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል ብለዋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ በተነሳ ግጭት 10 ሰው ሞተ


በቅርቡ በኢትዮጵያና የሶማሊያ የድንበር አካባቢ ከአስር ለሚበልጡ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግጭት ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት ተወካዮች በጅጅጋ ከተማ በመምከር ላይ መሆናቸው ተገለጠ። በኢትዮጵያ የሚገኙ ልዩ ሃይሎች በየጊዜው ከሶማሊያ አርብቶ አደሮች ጋር የሚያደርጉት ግጭት በድንበር ዙሪያ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ስጋት ውስጥ እንዳካተተው የሶማሊያ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። የሶማሌ ክልል መስተዳደር ባለስልጣናት በቅርቡ ለተፈጸመው ከ10 በላይ የሶማሊያውያን ግድያ የአል-ሸባብ እጅ አለበት ቢሉም የሃገሪቱ የጋልሙዱግ ግዛት ተወካዮች ግድያውን በታጣቂ ሃይሉ ሳይሆን በኢትዮጵያ ልዩ ሃይሎች መፈፀሙን እንዳስታወቁ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎም የሶማሊያው የጋልሙዱግ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አብደልካሪን ሁሴን ሌሎች የፀጥታ ሃይሎችን በማካተት ከኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር እየመከሩ መሆኑም ታውቋል። በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታም በድንበር ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እልባት ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ ሃላፊው አክለው አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በየጊዜው ድንበርን በመጣስ ወደ ሶማሊያ ለመዝለቅ የሚያደርጉት እርምጃ በድንበሩ አካባቢ የጸጥታ ስጋት ፈጥሮ መገኘቱን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮቹን በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር አሰማርቶ ቢገኝም በተለያዩ ጊዜያት የተናጥል ወታደሮችን ወደሶማሊያ በማስረግ ከአልሻባብ ጋር ውጊያን እንደሚያካሄዱም የሶማሊያ ባለስልጣናት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል። ይሁንና ወታደሮች በድንበር በኩል የሚያደርጉት ጉዞ ከአርብቶ አደሮች ጋር ግጭት ውስጥ እየከተታቸው መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።

ከአውሮፓ ኢትዮጵያ ኑሮውን ለማድረግ የገባው ወጣት በሳንጃ ተወግቶ ተገደለ


በፈትያ አንዋር
ዓመት በዓል ከመድረሱ ሳምንት በፊት ጀምሮ የተለያዩ ውክቢያዎች፣ ፈንጠዚያዎች እንዲሁም ደስታና ሳቅ፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ ሀዘንም ሊኖር እንደሚችል እሙን ነው፡፡
ባሳለፍነው የፋሲካ በዓል ዋዜማም በጣም አስደንጋጭ ነገር ተፈጥሯል፡፡ መቼም ሰው ነንና በበዓል ዋዜማ ደስታችንን ለመግለፅ ወደተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ማምራታችን የማይቀር ነው፡፡ በዋዜማው በአዲስ አበባ መብራት ሀይል ኮንዶሚኒየም ውስጥ ሁለት የዛው አካባቢው ነዋሪዎች ሊዝናኑ በወጡበት ባልታሰበ ፀብ በሳንጃ የአንደኛው ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሌላኛው ደግሞ ሳንባው ተወግቶ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በህክምንና ላይ ይገኛል ፡፡

ሱዳኖች በድጋሚ ድንበር ጥሰው በመግባት 67 ኢትዮጵያውያንን አፍነው ወሰዱ!


ንጉስ ሃይለስላሴ ፋሺስቱ ጣሊያን እንደተሸነፈ ከስደት በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ነጻነታችንን በማወጅ ሰንደቅ ዓላማችንን በክብር የሰቀሉበት ቦታ ነው።
ህወሀት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ስር ባደረጋት መተከል ዞን የሚገኝ ታሪካዊ ቦታ ነው።
ዘንድሮ የሱዳን ወታደሮች መፈንጪያ: የኢትዮጵያውያን የስቃይ ቦታ ሆኗል። ትላንት ከአከባቢው በደረሰን መረጃ የሱዳን ወታደሮች ከቅዳሜ ጀምረው በመተከል ዞን ጎባ ወረዳ ኦሜድላ ቀበሌ ሰርገው በመግባት ኢትዮጵያውያንን ደብድበዋል ። በርካታ መኖሪያ ቤቶችን አፍርሰዋል። የእርሻ ቦታዎችን አቃጥለዋል። ህዝባችንን በገዛ ሀገሩ አርባ ገርፈውታል። ንብረቱን ቀምተው ወስደዋል ። እስከአሁን በህይወት ላይ የደረሰ የሞት አደጋ ባይኖርም 67 ኢትዮጵያውያንን አፍነው ወስደዋል። ጥቃቱ እስከእሁድ ምሽት ቀጥሎ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
የሱዳን ወታደሮች ድንበር ተሻግረው ሲመጡ: ኢትዮጵያውያንን ሲያሰቃዩና አፍነው ሲወስዱ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በቅርበት ነበር። ሪፖርትም ተደርጎለታል። ለኢትዮጵያውያን የሚደርስም ሆነ ከሱዳኖች ዱላና አፈና የሚያስጥል ግን የለም።
By Mesay Mekonnen

Monday, May 2, 2016

Etiopiska Socialdemokratiska föreningens medlemmar tillsammans med andra etiopiska demonstranter är vi framme på Norra Bantorget. Nu väntar vi på Karin Wanngårds tal och huvudtalaren Carin Jämtin(S) partisekreterare för socialdemokraterna

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደኢትዮጵያ እየተላለፉ መሰጠታቸው አሳስቦኛል አለ


ኢሳት ዜና- የኬንያ የደህንነት ሃይሎች በሃገሪቱ የፖለቲካ ጥገኝነትን ፈልገው የሚሰሰዱ ኢትዮጵያውያንን ለኢትዮጵያ መንግስት እያሳለፉ መስጠታቸው አሳስቦት እንደሚገኝ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። ይኸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ኬንያ መዲና ናይሮቢ ድረስ በመጓዝ ከኬንያ አጋሮቻቸው ጋር በመተባበር ድርጊቱን እየፈጸሙ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ይፋ አድርጓል።
ባለፉት አራት ወራቶች ብቻ በኬንያ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁ 25 ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ተላልፈው የተሰጡ ሲሆን፣ የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ መምሪያ ድርጊቱን እንዳስተባበለ ዘስታር የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ የፖለቲካ ስደተኞችም አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች ሲሆኑ፣ በቅርቡ በክልሉ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በርካታ ወጣቶች ወደጎረቤት ሃገራት እንዲሰደዱ ማድረጉን የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ቅሬታን ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ በእስር ቤት መሞታቸውም ይታወቃል።
ድርጊቱ አሁን ድረስ መቀጠሉን ያስታወቁት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የስደተኞች ኦፊሰር የሆኑት ቢላቶር ኒያምሪ በርካታ ቤተሰቦች የጠፉ ሰዎች ስለመኖራቸው አቤቱታን እያቀረቡ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በኬንያ ከ160ሺ በላይ ስደተኞችና የፖለቲካ ጥገኛ ፈላጊዎች እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል። የኬንያ የፓርላማ አባላት የሃገራቸው የደህንነት ሃይሎች ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የፖለቲካ ስደተኞችን ወደሃገራቸው መመለሳቸው አግባብ አይደለም ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸውም የሚታወስ ነው።
የኬንያ መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ገንዘብን በመመደብ የፖለቲካ አባላትን መልሶ ለመውሰድ ከኬንያ የደህንነት ሃይሎች ጋር በድብቅ እንደሚሰራ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸውም ይታወቃል።
የኬንያ ባለስልጣናት ድርጊቱን ቢያስተባብሉም የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽን ከመስጠት ተቆጥቦ ይገኛል።